ተቀደሰ ስብእና ለፖለቲካችን /ካለፈው የቀጠለ/
ጥላሁን ዛጋ
የዚህን ሃሳብ /idea/ እንዴትነት ለመግለጽ ባለፈው ጦማሬበግርድፉ የዳሰስኳቸው ባለታሪኮች ከዛሬ ሶስትና አራት ሺህ አመታት በፊት የነበሩ በእስራኤል አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና፣ መንፈሳዊ እሴቶች ላይ ጉልህ ሚና የተጫወቱትን ሰዎች ግለ ታሪክ የነጥብ ያህል የተጠቀምኩበት ዳሰሳ ነበር፣ይህንም ካለፈው ጽሁፌ የቀጠለ ላድርገውና አስፍተው /አምልተው/ ለሚጽፉ ልሂቃን ወይም በጉዳዩ ላይ በስፋት ለመጻፍ ሃሳቡ ላላቸው የማሪያም መንገድ ልስጥ፦
የሰው ልጆች የተሰጣቸውን የእድሜ ገደብ አጠናቀው ከሚኖሩባት ምድር እስኪሰናበቱ ከሌሎች እንስሳት በተለየ መልኩ በማህበራዊ አብሮነት ይኖራሉ፣ ይህ አብሮነት በተናጠል እኔነት ውስጥ የጋራ ቁስ ወይም ሃሳብ እንዲኖራቸው ያስገድዳል፣ በመሆኑም ይህን የጋራ የሆነ አስተሳሰብ ወይም ቁስ በጋራ የመጠቀም ፋይዳው አልያም በጊዜ ተወስኖ ያለግጭት የመጠቀሙ ሂደት በጋራ በሚያዳብሯቸው ባህላዊና ወጋዊ ድንጋጌዎች ማዕቀፍ ውስጥ ተወስነው ይቆያሉ፣ ይህ አብሮነት ከቤተሰብ ወደ ማህበረሰብ ከዚያም ወደ ሀገር ያድግና ቤተሰብ ውስጥ የተመሰረቱት ወግ፣ ባህል፣ እምነትና፣ ተግባቦታዊ እሴቶች ወደ ሃገራዊ ህግጋት ይቀየራሉ፣ እነዚህ ህግጋት በሃገር ደረጃ /ብዙሃን ማህበረሰብን/ በቀጥታ ለመዳኘት ባለው ማህበረሰብ ቁጥር የተወሰነ ይሆናል፣ ለዚህም ነው ይህ የማህበረሰባዊ ሳይንስ ዘርፍ የሆነው ፖለቲካ /political science/ ለአንድ ማህበረሰብ ወሳኝና መሰረታዊ የሆነው
ስለዚህ የሰው ልጅ በኑሮው ለአመታት አብሮት ያደገው ባህል፣ ወግ፣ እምነትና ማህበረሰባዊ ህግጋት ብሎ ያስቀመጣቸው እሴቶች የተጣሱ ሲመስለው ያኮርፋል፣ ይቆጣልከዚህ በተጨማሪም መሰረታዊ የተፈጥሮ መብቱም ሲነካ እንዲሁ ያምፃል፣ ይሸፍታል(በልብም፣ በእግርም) ራሱን ብሎም የራሱን ማህበረሰቦች ነፃ ለማውጣት መብቱን ለማስከበር ይታገላል፣ ይህ አላማው ለሞት የሚያደርሰውም ቢሆን ራሱን ይሰጣል፣ ይህ እንግዲህ ለራእይ መሳካት ያለ ቁርጠኝነት ቅዱስና ተፈጥሮአዊ ሀብት ነው፣ ለመብት መታገል፣ ለራእይ መሰዋት፣ ስለ ትግሉ ራስን መስጠት፣ አብሮ ካደገና ከተቀረፀ ስነ-ምግባራዊ እሴት የሚፈልቅ ነው
ባለፈው ፅሁፌ ላይ ከነፃነት ትግሉ ባልተናነሰ(ምናልባትም በሚልቅ) መልኩ የታጋዮችን ስብዕና ቅርፀት መንፈሳዊ የእድገት ደረጃ ልቀት፣ ለአላማ መሳካት ባለ ፅናትና ቁርጠኝነት ዙሪያ ከዘመናት በፊት የነበሩ ሕዝባዊ መሪዎችን አርአያ (ዋቢ) አድርጌ ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ፣ እነዚህ መሪዎች ታሪካቸው እንደሚያስረዳን ከፈጠራቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት(ጠበቅ ያለ በመሆኑ) ህዝባቸውን እንዲያፈቅሩ፣ ሀገራቸውን እንዲወዱ፣ ከህዝብ ፊት የነፃነት ፋና ወጊዎች በመሆን አርአያነት ያለው ሥራ ሰርተዋል፣ “ይህን ሕዝብ ከምታጠፋ እኔን ከሕይወት መዝገብ ሰርዘኝ” በማለት ስለህዝብ የመሞትን ፅናት ያስተማረን ሙሴ፣ “ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ—ባላስታውስሽ ምላሴ ከጉሮሮዬ ትጣበቅ” ብሎ ፍፁም የሀገር ፍቅርን ያሳየን ዳዊት ለተቀደሰው የፖለቲካ ስብዕና ተምሳሌት ከዘመናት በፊት የነበሩ የሩቅ ትውስታዎች ሲሆኑ፣ በዘመናችን በቅርብ ርቀት ተከስተው ካለፉትና በሕይወት ካሉት የምናያቸው የትግል መሪዎች ደግሞ በአርአያነታቸው ዘወትር የምናወሳቸው በተቀደሰው የፖለቲካ ስብዕና ህዝብን መማረክ ጠላትን ደግሞ ማሸነፍ የቻሉ ናቸው
“i have a dream-ሕልም አለኝ”
የጥቁር መብት እንደመብት በማይቆጠርበት፣ በቆዳ ቀለም ሰዎች መብታቸው በሚሸራረፍበት ጨለማው ዘመን የተወለደው ማርቲን ሉተር (jan.15 1929) የሲቪል መብቶች ተሟጋች፣ ፖለቲከኛ እንዲሁም በአቤኔዘር መጥምቃውያን ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰባኪ፣ መምህርና አጥማቂ የነበረ ሰው ነው፣ ብሩህ የፖለቲካ ርዕዮት እንዲሁም ማንነት ያላቸው መሪዎች ባለራእይ ናቸው፣ ለዚህ ነው ማርቲን “ሕልም አለኝ ” በማለት በ 1963 የፈረንጆች ፀደይ ወር ታሪካዊ የሆነ ንግግር አድርጎ በተለያየ መንገድ ተጨቁነው ነፃነታቸውን ተገፈው መብት ያጡትን የተገፉ ጥቁሮች በህብረት ያንቀሳቀሰበት የትግሉ ምዕራፍም በመላው ዓለም ትኩረት የሳበበት ነበር፣ ከዚህ ንግግር ቀደም ብሎ ባሉት አመታት ከኖርዝ ካሎራይና ተነስቶ እስከደቡባዊ የአሜሪካ ግዛቶች የተቀጣጠለ “sit-ins” የተባለ ሕዝባዊ አመፅ ወይም ቀደም ባሉት ጊዜያት ለጥቁሮች በተከለከለ ቦታ መቀመጥ በሚል የትግል እንቅስቃሴ “non-violent coordinating committee” በማዋቀር ትግሉን ሲመራም ነበር፣ በኅላም የትግሉ ውጤት አፍርቶ በ 1964 እ ኤ አ በመላዋ ዩ ኤስ ኤ ህገ-መንግስት ውስጥ የሲቪል-መብቶች (civil rights)መከበርን በተመለከተ የሕግ አንቀፅ ተደነገገ፣ አንቀፁም የጥቁር አሜሪካውያንን መብት በመጠኑም ቢሆን ከፍ ያደረገ ሲሆን ማርቲንም የሰላም የኖቤል ሽልማት በዚሁ ዓመት እንዲያገኝ ሆኖአል
ዴዝሞንድ ምፒሎ ቱቱ
የፀረ-አፓርታይድ እንዲሁም የጥቁር አፍሪካውያን የመብት ታጋይ ቱቱ የቤተክርስቲያን አገልጋይ፣ ዲያቆን(ካህን) የነበሩ ለጥቁሮች ነፃነት አርአያነት ያለው ተጋድሎ ታሪክ የፈፀሙ ታላቅ ሰው፣ የፀረ-አፓርታይድ እንቅስቃሴ በተቀጣጠለበት ዘመን (oct.7,1931) የተወለደው ቱቱ በወጣትነቱ በቤተክርስቲያን አገልግሎት የተጠመደ እንዲሁም በትምህርት ራሱን ያነፀ፣ ለጥቁር መብት ትግል ራሱን ሰጥቶ የኖረ በተቀደሰው የፖለቲካ ስብዕና ያደገ ሰው ነው፣ በ1958 በቅ/ጴጥሮስ ቲዎሎጂካል ኮሌጅ(ጆሃንስበርግ) የአገልግሎት ትምህርት ተምሮ የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ዲቁናን ተቀበለ፣ በ1960 ደግሞ ቅስናን ተቀበለ፣ ከዚህ በሁዋላ አርክ ቢሾፕ ዴዝሞንድ በመባል የዓለም አብያተ-ክርስቲያናት ህብረት ም/ቤት ሊቀ-መንበር ሆነው እያገለገሉ ሳሉ፣ ከዚህ አገልግሎት በተጨማሪም በፀረ-አፓርታይድ ትግል ቀጥታ በመሳተፍ ትግሉን ሲደግፉና ገዢዎችን ሲቃወሙ ኖረዋል።
በ1976 ቱቱ የመጀመሪያው የጆአንስበርግ አንግሊካል ዲን ሲሆኑ “ምናልባት እኔ የመጀመሪያው ጥቁር ተመራጭ ሆኘ ለዚህም በቅቼ ይሆናል፣ በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ይህ የትግላችሁ ውጤት ነው፣ ገና ይቀጥላል” በአንድ ስብሰባ ላይ በማለታቸው ተይዘው ለቀናት ታስረው ተለቀዋል፣ በተጨማሪም በ 1976 የሌሴቶ ግዛት ጳጳስ ሲሆኑ ለደቡብ አፍሪካ ጠቅላይ ሚኒስቴር የታሰሩት የመብት ተሟጋች ጥቁር እስረኞች እንዲፈቱ ደብዳቤ ፃፉ መልስ ባያገኙም፣ በ 1978 የደ/አፍሪካ አብያተ-ክርስቲያናት ም/ቤት ሆነው ተመረጡ፣ በዚህ ጊዜ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው በሀገሪቱ አፓርታይድ እንዲቆምና የፀረ-አፓርታይድ ትግሉ እንዲቀጣጠል ያስቻለ ታሪካዊ ደብዳቤ ፅፈዋል።
ከነሱ ምን እንማር ???
አሁን አሁን በተደጋጋሚ የሚጮህባቸው በተቃውሞ ጎራ ያሉ አንድ ያለመሆን፣ የመከፋፈል፣ የመገነጣጠል፣ የመበጣጠስ፣ ያለመቻቻል ችግሮች የፖለቲካችን ርኩሰት ውጤቶች ለመሆናቸው ነጋሪ አያሻንም፣ በዚህ ስብዕና ውስጥ ያሉ እሴቶች ያለመጠንከር እንዲያውም ከናካቴው ያለመኖር የፈጠረው ደንቃራ ነው። ለራእይ የመታመን እሴት፣ ምስጢር የሚጠብቅ የተገራ ማንነት፣ ሁሉን የማክበርና ቅቡል በሆነ ሠብዓዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ ስብዕና፣ ያለመኖር፣ በሰዎች ላይ የሚደርስን በደል በራስ እንደደረሰ አለመቁጠር፣ ግለሰባዊ ስግብግብነት፣ የፈጠራቸውና ከዚህም በባሰ መልኩ በባላንጣነት ቁርሾ የመመዳደብ ፍርጃ ላይ ዶሎናል፣ ከዚህ ከገባንበት አዘቅት ለመውጣት ጊዜው አሁን ነው፣ የአንድነት ቄዳር(ፀሎት) የፍቅር ጠበል ያስፈልገናል፣የተበላሸውንና የቆሸሸውን ትግል ለመቀደስ ስሜትን ማሸነፍ፣ ከእኔነት ይልቅ ሃገራዊ ማንነትን ማስቀደም፣ ታጋይ ጉዋድህ የትግል አጋርህ እንጂ ከፊትህ እንደቆመ ደንቃራ ያለመቁጠር፣ ትኩረትን ጠላት ላይ ብቻ ማድረግ፣ ለመለያየት በር ያለመክፈት፣ አንተ ያለህ ሁሉም ስሜት(የሀገር ፍቅር፣ የአላማ ቁርጠኝነት፣ ታማኝነት) ሌላውም ጋር ሊኖር እንደሚችል ማሰብ፣ ችግሮችን በግልፅና በቅንነት በመወያየት መፍታት፣ ይገባናል፣ በተለይም በሃይማኖት ላይ ያሉ የእምነት መሪዎቻችን ፈጣሪን በማመን ባለ ድፍረት ገዢዎችን ስለክፉ ስራዎቻቸው ሕዝብ ላይ ስለሚፈፅሙት ግፍ ሊገስፁ፣ ሊመክሩ፣ ሲገፋም ሊቃወሙ ይገባል፣ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል” እንዳለው ቅ/ጳውሎስ ከገዥዎች ሰይፍ ይልቅ የእግዚአብሔር ፊት ያስፈራልና፣ እውነትን በድፍረት ሊናገሩ ወቅቱ ያስገድዳቸዋል፣ ሕዝብ ሲገፋ ሲበደል ግንባር ቀደም ተሟጋች ሊሆኑ ይገባል፣ ለሕዝብ ማዘን ስለህዝብ ራስን መስዋዕት ማድረግ ከቀደሙት ይልቁንም ከኢትዮጵያዊው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ ሊማሩ ይገባል፣ ስለዚህ ሀገራችን የተጠማችውን ነፃነት ህዝባችን የተነፈገውን መብት ለማስመለስ የመጨረሻውን የትግል ምዕራፍ ለመወጣት የቤትስራዎቻችንን አሁን እናጠናቅቅ እያልኩ በመጨረሻ በፓትርያርክ ቱቱ ቅንጭብ የደብዳቤ ክፍል ፅሁፌን ብቁዋጭስ…???
“ወደነፃነት እየተጠጋን እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም፣ እውነት ብትደበቅም ከሐሰት በታች ግን በፍፁም ተቀብራ አትቀርም፣ ሙት ሕያው ይሆናል፣ ጨለማውም ያለጥርጥር ይነጋል!!!”
ትንሣኤ ለኢትዮጵያ… ድል ለተጨቆኑት!!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar