lørdag 18. mai 2013

ከአፋር ጋድሌ ጋር በተያያዘ ባለስልጣናትን እና ፖሊሶችን ጨምሮ 14 ሰዎች ታሰሩ


ከአፋር ጋድሌ ጋር በተያያዘ ባለስልጣናትን እና ፖሊሶችን ጨምሮ 14 ሰዎች ታሰሩ

ኢሳት ዜና:-ባለፈው ሳምንት ከአፋር ጋድሌ ወታደራዊ ንቅናቄ ጋር በተያያዘ  14 ሰዎች መታሰራቸውን፣ ከታሰሩት መካከልም፣ የቀበሌው ሊቀመንበር፣ የወረዳ ምክር ቤት አባል፣ አንድ ፖሊስ እና ሽማግሌዎች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሎአል።
አብዛኞቹ የተያዙት በፌደራል ፖሊሶች ሲሆን በቅርቡ 70 የሚሆኑ የአፋር ወጣቶች አፋር ጋድሌ የሚባለውን  የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ የሚገኘውን ድርጅቶች መቀላቀላቸውን ተከትሎ ነው።
ከታሰሩት መካከል የሩማይቶ ቀበሌ ሊቀመንበር ፣አቶ  አብዱሊ ሞሚን፣ አፈጉባኤው ኖር አሊ፣ የፖሊስ አዛዡን  ያዮ አሊ ፣  አብዱጀሊል አንፈሬ፣ ሙሀመድ አሊ፣ ሙሀመድ ኢሴይ፣ ሙሀመድ ዩሱፍ፣ አቦ አብዱ፣ ፎካ ሀሌ፣ ሀቢብ መሀመድ፣ አብዱል ሁሴን፣ የ70 አመቱ  የሱፍ አህመድ፣ እና አብዱ ኑር ይገኙበታል።
በጉዳዩ ዙሪያ የአፋር ጋዲሌ ወታደራዊ አዛዥ የሆኑትን ኮሎኔል መሀመድ አህመድን አነጋገርናቸው፣ ኮሎኔልም የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውንና አብዛዦቹ ከእርሳቸው ጋር ዝምድና ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል። አንዳንዶች የት እንደገቡም እንደማያውቁ ኮሎኔሉ ገልጸዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ በአፋርና በሶማሊ ሀውያ ጎሳዎች መካከል ትናንት በአዋሽ አርባ አካባቢ በተደረገ ከፍተኛ ውጊያ 5 አፋሮች ሲገደሉ 15 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል። ግጭት ከወር በፊት ከተካሄደው ግጭት ጋር የተያያዘ ነው። በሶማሊ ሀውያ ጎሳዎች በኩል የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልታወቀም።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስትን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የሶማሊ ክልል ሚሊሺያዎች ከክልላቸው አልፈው በአፋር ክልል ስለሚፈጽሙት ጥቃት የሚሊሺያ አዛዡን የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ አብዲን ለማግኘት  ሙከራ ብናደርግም አዲስ አበባ ለስብሰባ መሄዳቸውን ጸሀፊያቸው በመግለጽ ሳይሳካ ቀርቷል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar