tirsdag 21. mai 2013

አዘነ አሉ ጎጃም የበላይ አገር


አዘነ አሉ ጎጃም የበላይ አገር፤
ማቅ ጥለቱን ለብሶ እርቃኑን በክር፤
ዙፋን ሲጎናጠፍ ጐጠኛው ሲከብር፤
እራፊ አደሩበት በዘር መደውር፤
‘እንደ ማሪያም ጠላት’ ተባሮ እንዲኖር፤
ጐጆው እንዳይጠና ተሳዶ በዙር፤
በእምነቱ እዳ ከፋይ ለአገሩ ድንበር፤
አርባ ተገረፈ በክህደት መንደር፤
በደሙ በአጥንቱ በዘሩ በትር፤
ማዕት አወርዱበት ሰው እንዳልነበር፤
በቆዳው አለንጋ በዓይኖቹ ስንጥር፤
ገርፈው ያጠቁታል ታግሶ ቢያድር፤
የቀን በለሶኞች ሊያክስሙት ከምድር፤
ሃያ ዓመት ሲወጉት እትብት አምካኝ ዘር፤
ዳግም በላይ ላይዘልቅ ከትበው ነፍሰ ጡር፤
አድባሩን አርክሰው በወንድ ደንገጡር፤
ሺህ ጭንጋፍ አንጋግተው ሆዳም ከርስ ጉጥር፤
አልወለድ ብሎ አንድ በላይ ለአሳር፤
ጎጃም አዘነ አሉ ማህጸን ሲቀብር። 
ጥምጥም ትጥቁን ፈቶ ሌጣውን ሲያድር፤
በጨለማ ሲጋዝ በቀን ሲደፈር፤
ዋስ የለው ጠበቃ እድሜ ልክ አሳር፤
የፊታውራሪ አበሻ የመጃሌ አድባር፤
ካባ ሸማ ልብሱ የክት የሐገር፤
በርኖሱን ማን ለካው? የነጩን ግብር፤
ለሰንደቁ ሙቶ በአጥሙ አጥሮ ድንበር፤
እንቅልፍ ሰላም ነሱት የጓዳ አይጦች ሸር፤
የተዳፈነ እሳት ከእምድጃው ሳይጭር፤
ይዞታው ቢቆጨው የቤቱ አባወራ ምሰሶው ማገር፤
አዳራሹን ለቆ ውጭ በረንዳ ቁር፤
ተፈራረቁበት ውግዘትና ስደት ጥቃት ቸነፈር፤
አዘነ አሉ ጎጃም ማቅ ለብሶ ጥላሸት የኮስትር አገር። 
በሸብል በረንታ በእነማይ ምድር፤
አጥሙ መሬት ሲያርድ የሺፈራው ጦር፤
ሙሉ ጎጃም ቢያንጥ ጋራው ሸንተረር፤
አረንዛው ዳሞቴ ፋኖው አቸፈር፤
እነብሴና እነሴ ቢቸና ሳር ምድር፤ማርቆስ አገው ምድር፤
እንኳንስ ለጓዳ ግድግዳ እሚቆሙ ለኢትዮጵያ አጥር፤
ዛሬ ግን ተጋዙ የፍጥኝ ተሳስረው በእፉኝት መንደር፤
ቢያጠቃም ቢያጠቁት ኪሳራው ለአገር፤
ቆርጠው በማይጥሉት የእጅ ቁስል ኪንታር፤
ሕመም የውስጥ ደዌ አንጀት አሳርር፤
የትውልድ ጸብ ቁርሾ መርገምት ውል እድር፤
ሰብዕን የሚያመክን አረማሞ ዘር፤
አድዋው ገኖበት ሰብል አብቃዩ አፈር፤
ሳማ አረም ቢወረው የጀግኖች መቃብር፤
አዘነ አሉ ጎጃም አልቦው ባለአገር። ፈርዶበት ወያኔ ግዞት ቁም አሳር፤
ቁልቋል እያስወጋው በዘር እሾህ አጥር፤
የአማራ ደም አጥንት እሚያብጠረጥር፤
ከእርስቱ ከቤቱ ከአገሩ እንዳይኖር፤
ሃያ ዓመት ሲያስግዘው አዋክቦ በጦር፤
ባንዳ የባንዳ ልጅ የፋሽስት አሽከር፤
ዜጋ እያሳደደ ባዕዳንን ሲያከብር፤
ኩርማን አያጋራም እሸት አያዞር፤
ከጣሊያን መስጥሮ ወንዛችን ቢያቁር፤
አርቆ መቀመቅ ጦስ እሚቆፍር፤
አባይን አስግሮ ጊዮንን ሊቀብር፡፡ 
ንገረው ለጐንደር ለቴዎድሮስ ልጅ፤
ተነስ ታጠቅ በለው ሃዝን ለቅሶ አይበጅ፤
የክፉ ቀን ደራሽ ደመላሽ ነው እንጅ፤
ለወሎም ላኩበት ደሴ ወራይሉ ከሚሴ መሽጉ፤
የባንዳን መሹለኪያ በራበሩን ዝጉ፤
ሸዋ መሃል አገር አዲስ አቦች ንቁ፤
ወያኔው እንዲያዝ ከነቀለብ ስንቁ፤
ሐረር ሃዲድ ዝጋ አፋር ጀግናው ውጣ፤
ወለጋና ከፋ ግስግሶ እስኪመጣ፤
ደቡብም በመላው ፈጥነህ ድረስ ቶሎ፤
ትግራይ ሸክሙን ያውርድ እርሙን ተገላግሎ፤
ለወገኑ እንዲደርስ በአንድነት ሆ! ብሎ፤
ኢትዮጵያዊ ያብር መሃል - ዳር ወጥሮ፤
ነፃነት ይቀዳጅ በትግል ተባብሮ፤
አንድ ቤት! አንድ ሃገር! ኢትዮጵያ ዘንድሮ፤
ጎጃም አዝኖ አይቀርም ይነሳል ፎክሮ። 

የጐንቻው! yegonchaw@yahoo.co.uk

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar