ያለንበት ጊዜ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆን ትረጉመ-ቢስ የሆነበት ደረጃ ላይ እየደረሰ እንዳይሆን የሚያሰጋበት ወቅት ነው። ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያዊነታቸው ሊከበርላቸው የሚገባውን የዜግነት መብት እየተነፈጉ ነው። መንግሥት የዜጎችን መብት ማስከበር ተስኖታል። ይህንን አስመልክቶ የኢሮብ መብት ተማጓች ማህበር (ኢ.መ.ተ.ማ) ተደጋጋሚ እሮሮዎችን ሲያሰማ የቆየ ቢሆንም አድማጭ ጆሮ ተነፍጎት ቆይቷል።
ከአንድ መቶ በላይ የኢሮብ ተወላጅ ኢትዮጵያዊያን በሻዓቢያ ታግተው ከተወሰዱ ይኸው አሥራ ሶስት ዓመት ሊሞላ አንድ ወር ቀርቶታል። ኢ.መ.ተ.ማ የነዚህ ዜጎች እጣ ፈንታ እንዲጠይቅ እንዲሁም የኢሮብ ሕዝብና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለሺ ዓመቶች የኖሩበት መሬታቸው ለኤርትራ መከለሉን በተመለከተ ለኢትዮጵያ መንግሥት ተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርብም፤ መንግሥት ጆሮ ደባ ልበስ ብሎ መቀመጥን መርጧል። ቀጥሎም በ2003 ዓ.ም ሻዓቢያ እንደገና በወርቅ ማምረት ላይ ተሠማርተው የነበሩ ከ260 በላይ ኢትዮጵያዊያን የትግራይ ተወላጆችን ከምእራብ ትግራይ ጠልፎ በመውሰድ ድኳቸው አጥፍቷል። ሆኖም፤ መንግሥት የነዚህን ዜጎች ደህንነት ለማረጋገጥና የሚገኙበት ሁኔታን ለማጣራት የወሰደው አንዳችም እርምጃ የለም። በተቃራኒው፤ አንዳንድ የኢህአዴግ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ኃይሎች በክስተቶቹ መንግሥት የመረጠውን ዝምታ በማውገዝ የአቋም መግለጫዎችን አውጥቷል። በውጭ ዜጎች መጠለፍ ወታደራዊ እርምጃ እስከመውስደ የተሯሯጠ መንግሥት ታግተው ደብዛቸው ስለጠፉ ዜጎቹ ምንም ዓይነት የሀላፊነት ስሜት አላሳየም የወሰደው እርምጃም የለም።
ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን የማፈናቀል አባዜ እጅግ አስከፊና ዘግናኝ በሆነ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል። መፈናቀሉ መልከ ብዙ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ለም የእርሻ መሬቶችን ለህንድና ለዓረብ ባለሀብቶች በስመ-ኢኒቨስትመንት ለመስጠት በሰበብ አስባቡ ከኖሩበት ቀዬ የሚፈናቀሉ ወገኖች ቁጥር እጅጉን ተበራክቷል። የከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በሰበብ አስባቡ ያለምንም ቅድመ ዝግጅት በዓቅማቸው ቀልሰው ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬ በማፈናቀል፤ ያለ ምንም ካሳ ቤቶቻቸውን በማፍረስ ሕጻናት፤ ነብሰ-ጡሮች፤ አሮጊት እናቶች፤ ሽማግሌ አባቶችና አቅመ ደካሞች ለሜዳ ኑሮ መዳረጋቸውን ታዝበናል። በተቃራኒው፤ መቐለ ውስጥ እንደታዘብነው ቤት እንዳይሠራባቸው በሕግ የተከለከሉና ለመናፈሻና ለደን እንዲጠበቁ በከተማው አስተዳዳሪዎች የተወሰኑ ቦታዎች ላይ የሥርዓቱ ባለሥልጣናትና የሥርዓቱ ታማኞች ሕግ ተላልፈው ፎቆችና ቪላዎችን ሲያሰሩ፤ በሕገ-ወጥ መንገድ የተሰሩ ናቸውና መፍረስ አለባቸው ብሎ የሚያፈርስ ቀርቶ፤ ሕግ ተላልፋቹሀል ብሎ የሚናገር ባለሥልጣንን ለመስማት አልታደልንም። ይህ በመቐለ የተከሰተው ዓይነት አሠራር በሌሎች አከባቢዎችም ተፈፅሞ ሊሆን ይቻላል። ሆኖም ለጊዜው መቐለ ላይ የተጣሰ ሕግ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥም እንደተጣሰ ለማመሳከር የሚያስችል ጭብጥ ስለሌለን በዚሁ ልናልፈው መርጠናል። እነዚህ ከላይ ያነሳናቸው ጭብጦች ላይ ተመርኵዘን በመከሰት ላይ ያለውን ህዝብን የማፈናቀል ተግባር አስፈላጊ ሆኖ እንኳ ቢገኝ ብቁ ቅድመ ዘግጅት ተደርጎ እንዲካሄድ የማድረግ ሓላፊነት ለመሸከም የሚችል መንግሥት እንደሌለን የሚያመላክት ሆኖ እናገኘዋለን። በየጊዜው በሻዓቢያ እየታገቱ ለሚወሰዱና ደብዛቸው ለጠፋ ዜጎች መቆም ያቃተው መንግሥት እንዳለን ከታዘብንም ሰነባብተናል።
አሁን ይህንን አጭር መግለጫ ለማውጣት ያስገደደን እጅግ አስደንጋጭና በዓይነቱም ለየት ያለ ኢትዮጵያዊያንን ለዓመታት ከኖሩበት መሬት የዘር ሐረጋቸው እየተመረጠ አፈናቅሎ የማባረር ኢትዮጳዊነትን የሚፈታተን ተግባር ሲፈጸም መታዘባችን ነው። ከዚህ በፊት ኢትዮጵያውያን ዘራቸው እየተጠና ከጉራ ፈርዳ ተፈናቅለው መባረራቸውን ሰምተናል አንብበናል። ያንን ስንሰማና ስለዛ ስናነብ እጅጉን የደነገጥን ቢሆንም፤ አገዛዙ ከዚህ ስሕተት ተምሯል የሚል ግምት አሳድረን ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ተመሳሳይ ስሕተት እንደገና በተመሳሳይ መልኩ ተደግሞ ተከስቷል። አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊያን ከበንሻንጉል ጉምዝ ፍጹም ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እንዲባረሩ ተደርጓል። በዚህም፤ የኢህአዴግ መንግሥት በጉራፈርዳ የፈጸመውን ኢሰብአዊ ግፍ ከመድገም ወደ ኋላ እንደማይል በሚገባ እንድንረዳ አስችሎናል። ስለሆነም፤ ሁኔታው እጅጉን አሳስቦናል። ኢትዮጵያዊያን በዘር ሐረጋቸው ምክንያት ከተወሰነላቸው ክልል ውጭ መኖር የማይችሉበት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ሲቀጥል ታዝበናል። ይህ ዛሬ በአማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ዘግናኝና አሳፋሪ የማፈናቀል ተግባር፤ ነገ በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ላይ ላለመቀጠሉ ምንም ዓይንት ዋስተና የለም። ይህ በእንዲህ ከቀጠለ ደግሞ ኢትዮዽያና ኢትዮዽያዊነት ምን ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ህሊና ያለው እያንዳንዱ ኢትዮዽያዊ ቆም ብሎ ራሱን መመርመር ይኖርበታል ብሎ መኢተማ ያምናል። በመሆኑም፤ በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ፤ ኢትዮጵያዊያንን ከቅያቸው የማፈናቀል ተግባር እንዲያቆም ኢትዮጵያዊያን ተባብረን የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። የኢህአዴግ አገዛዝም፤ ህዝብን የማፈናቀል ተግባር የሚያስከትለው መዘዝ ምን ያህል አስከፊና አውዳሚ ሊሆን እንደሚችል በወጉ ለመገንዘብ ያለመፈለግን እልህ ማቆም ይጠበቅበታል። ካልሆነ ግን በሂደት ላገሪቱም ሆነ ለራሱ ለኢህአዴግ አላስፈላጊ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል በወቅቱ ቢገነዘበው የተሻለ ይሆናል።
ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደፈለጉ በፈለጉበት ቦታ ተዘዋውረው ሠርተው ሀብት ለማፍራት፤ ወልደው ከብደው ለመክበርና በገዛ አገራቸው ውስጥ ያለምንም መሳቀቅና መፍራት የመኖር ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትና ከሌላቸው ኢትዮጵያ የምትባል አገርና ኢትዮጵያዊ የሚባል ዜጋ ሊኖር ይችላል ብሎ ለማሰብ የሚቻል አይሆንም። ይህ ማለት ግን መንግሥት በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖረውን የመሬት ይዞታ መልክ ለማስያዝ የሚረዳ ፖሊሲ መንደፍ የለበትም ለማለት እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ለደን ልማት፤ ለመናፈሻ፤ ለዱር አራዊት፤ ለእርሻ፤ ለኢንዳስትሪ፤ ለመኖርያ፤ …….ወዘተ የሚሆኑ ቦታዎች ተለይተው አይከለሉ ለማለት አይደለም። መከለል አለባቸው። አሠራራችንም ሆነ የአመራረት ዘየቤያችን ዘመናዊ ማድረግ ላይ ተቃውሞ የለንም ብቻ ሳይሆን የምንደግፈው ጉዳይ ይሆናል። ሆኖም፤ የድሀው ህዝባችን ኑሮ በማያመሰቃቅልና ዜጎችን በማይለያይ መልኩ በጥናትና በጊዜ እየተለየ መከናወን አለበት ብለን እናምናለን። የማናምነውና ፍጹም የማንቀበለው ጉዳይ ቢኖር ግን የተለያዩ የክልል ትናንሽ ንጉሶችን በመፍጠር ኢትዮጵያዊንን ከኛ ዘር ስላልተወለዳችሁ፤ ይህ ክልል የነ እገሌ ዘሮች የትውልድ ክልል ስለሆነ ወይም ስላልሆነ ከሌላ ቦታ የመጣቹህ ወይም ከሌላ ዘር፤ ወገን የሆናቹህ በዚህ ክልል፤ መንደር፤ ሰፈር…ወዘተ መኖር አትችሉም የሚለው አካሄድ ኢትዮጵያዊነትን የሚንድ አደጋ አለው ብለን በጽኑ እናምናለን። አንድ ኢትዮጵያዊ በአንድ ክልል ውስጥ መጥቶ መኖር ሲጀምር፤ መኖርያውን በሚቀይስበት ጊዜ የመፍቀድም ሆነ የመከልከል ሥልጣን በሕግ የተሰጠው ኣካል ሲከለክልም ሆነ ሲፈቅድ የተገልጋዩን የዘር ሐረግ መስፈርት እንዳይጠቀም በሕግ መከልከል ይኖርበታል እንላለን። አንድ ኢትዮጵያዊ በተወሰነ ቦታ ላይ የተወሰነ ሥራ ለማከናወን ሲፈልግ፤ ያ ቦታ እንዲሰጠው ለመፍቀድም ሆነ ላለመፍቀድ አስቀድሞ በተቀመጠው ፕላን መሠረት በሚቀመጥ መስፈርት እንጂ ግለሰቦች በዘፈቀደ በሚዘውሩት መስፈርት ሊሆን ፈጽሞ አይገባም። ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ ዘርና ወገን እየተለየ ኢትዮጵያዊያንን ማፈናቀል እየገፋ ሲሄድ ማቆምያ ድንበር ሊበጅለት የማይቻልበት ደረጃ ሊደርስ እንደምችል መታወቅ አለበት። የዚህ ድምር ውጤት በጋራ መልማትና ማደግ ሳይሆን ተያይዞ መጥፋትን እንደሚያስከትል መጠርጠር የለበትም። የኢትዮጵያ ህዝብ በየክልሉና በየመንደሩ ተከልሎ እንዲኖር የተወሰነ ዕለት እንደዚህ ዓይነት ችግር እንደሚከተል በግልጽ የሚታወቅ እንደመሆኑ መጠን፤ የሚያስከትለውን ችግር ለመረዳት የሚከብድ አልነበረም። በመሆኑም፤ አሁን እያየነው ያለ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ መፈናቀል እንዲከሰት ሆን ተብሎ የታቀደ ፀረ አንድነትና ኢትዮዽያዊነት ተግባር መሆኑም ግልጽ ነው።
በየክልላችን ተወስነን እንድንኖር የተደረገ ዕለት አብሮና ተማምኖ የአገራችንን ዳር ድንበር ለማስከበር የሚቆም ብሔራዊ ሠራዊት አይኖረንም። ለይስሙላ የሚቋቋም ብሔራዊ መከላከያ ኃይል ሊኖረን ይችል ይሆናል። ያ ግን መለዮ የለበሱ ሰዎች ስብስብ እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሠራዊት ሊሆን አይችልም። በኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜት ተኮትኵቶ፤ የችግሯን ገፈት አብሮ ለመቅሰም አብሮ የመሰለፉን ያህል ከጥቅምዋም አብሮ እኩል ለመቋደስ የማይችል ወታደር ብሔራዊ ወታደር ሊሆን አይችልም። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ በቅራኔ በተወጠረ ቀጠና ውስጥ ላሉ አገሮች ቀርቶ አንጻራዊ ሰላም አላቸው በሚባሉ አገሮች ውስጥም ቢሆን ተቀባይነት የለውም። የሠራዊቱን ጉዳይ አነሳን እንጂ በየመስኩ ብንዘረዝረው ሊያስከትለው የሚችለው ውድቀት የት የሌለ ጥፋት እንደሚሆን ለመገመት የሚከብድ አይደለም። በመሆኑም፤ አሁን አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ መጀመርያ በኢትዮጵያዊ ወገንተኝነታችን እንዲሁም ሰው በመሆናችን እጅጉን አሳዝኖናል። በመሆኑም፤ ይህንን አስነዋሪ ተግባር እያወገዝን የነዚህ ዜጎች ጉዳይ ከግብር ይውጣ አሠራር በዘለለ ወደ ተፈናቀሉበት ቀዬ ተመልሰው እንዲኖሩ እንዲደረግና ለደረሰባቸው የአካል፤ የንብረትና የሥነ-አእምሮ ድቀት ተገቢ ካሳ እንዲያገኙ እንዲደረግ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ከዚህም በተጨማሪ፤ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለኢፈዴሪ ፓርላማ በሰጡት መግለጫ ተግባሩን ማውገዛቸው የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም፤ ማውገዝ ብቻውን የሚፈለገው ውጤት ሊያስጨብጠን እንደማይችልና የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረ-ሰብ በቀላሉ የሚቀበሉትና የሚጃጃሉበት እንደማይሆን ይረዱታል ብለን እንገምታለን። ስለሆነም፤ ኢትዮጵያዊያን በዜግነታቸው ተማምነው ሕጋዊ ዋስትና እንዳላቸው እርግጠ ኛ እንዲሆኑና አገራችን በዓለም አቀፉ ህብረተ-ሰብ የተሰጣትን ገጽታ ወደ በጎነት ለመቀየር ይቻል ዘንድ ባስቸኳይ ሕጋዊ የእርምት እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። በኢ.መ.ተ.ማ እይታ ይህ ጉዳዩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት “የተወሰኑ ኪራይ ሰብሳቢ የወረዳ አስተዳዳሪዎች” የፈጸሙት ነው የሚለው አባባል በአመክንዮ ሊደገፍ የሚችል አይደለም። ቢያንስ ከፍተኛ የፈደራል የመንግሥት ባለሥልጣኖች በወንጀሉ ውስጥ አለመሳተፋቸው በእርግጠኝነት ከታወቀ፤ በጥልቀት ሊመረመር የሚገባው የሕግ ሕፀፅ መኖር አለበት። ካልሆነ ግን ማንም የወረዳ አስተዳዳሪ ከባዶ ተነስቶ ይህን ያህል ህዝብ የማባረር ሥልጣን ይኖሯል ብሎ ለማሰብ እጅጉን ይከብዳል። ስለሆንም፤ ችግሩን ከሥሩ በማጥራት በነዚህ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው አስከፊ በደል በማያዳግም መንገድ እልባት እንዲያገኝና ኢትዮጵያዊነት ከመጠውለግ ድኖ እንዲያብብ ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ አንዲታገል አጥብቀን እንጠይቃለን።
ኢትዮጵያዊነት በኢትዮዽያዊያን የጋራ ትግል ይለመልማል!!!
የኢሮብ መብት ተማጓች ማኅበር (ኢ.መ.ተ.ማ)
ግንቦት 2005 ዓ.ም

Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar