በአትዮጵያ የሚታየው የሀኪሞች እጥረት እየጨመረ ነው
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጽያ ሐኪሞችን የማሰልጠኑ ስራ ከታሰበው ግብ አኳያ አፈጻጸሙ ደካማና አሁንም የባለሙያ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ እየታየ መሆኑን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘ ሰነድ አመለከተ፡፡
በጤና ዘርፍ ከሰው ኃይል አኳያ ከፍተኛ እጥረት እየታየ ያለው በሐኪሞች፣በአዋላጅ ነርሶች እና በሰመመን ሰጪ ነርሶች ደረጃ ያለው ነው ያለው ሰነዱ ባለፉት ጊዜያት በመደበኛ ፕሮግራም ሐኪሞችን ለማሰልጠን የሚወስደው ጊዜ ረጅም ከመሆኑና ሥልጠናውን የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥርም አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ ማሰልጠን የቻለችው የሐኪሞች ቁጥር በጣም አነስተኛ እንደነበርና ያሉትም ባለሙያዎች ቢሆኑ የተሻለ ጥቅማጥቅም ፍለጋ ሃገር ጥለው የሚሰደዱ በመሆናቸው ችግሩን መቅረፍ ሳይቻል መቆየቱን ያትታል፡፡
በመሆኑም አንድ ሐኪም ለ10ሺ ህዝብ ጥመርታ ለማድረስ ቢታቀድም በአሁኑ ወቅት ግን አንድ ሐኪም ለ30 ሺ158 ሕዝብ ጥምርታ ሆኗል፡፡
ይህ ከስታንዳርዱ በታች የሆነ አፈጻጸም ለማስተካከል አዲስ ስርዓተ ትምህርት በማዘጋጀት በጠቅላላው በ27 አዲስና ነባር ዩኒቨርሲቲዎች ከ9 ሺ በላይ ሐኪሞች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ሰነዱ ያብራራል፡፡
የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ በወሊድ ወቅት የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመቆጣጠር በመካከለኛ ደረጃ ባሉ የጤና ባለሙያዎች ለማሟላት የጤና መኮንኖችን በተቀናጀ የድንገተኛ የማህጸንና ጽንስ ቀዶ ህክምና አሰልጥኖ በማሰማራት ክፍተቱን ለመሙላት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡
እስካሁን 43 ባለሙያዎች ስልጠና መከታተላቸውን በአሁኑ ወቅትም 489 ያህሉ በስልጠና ላይ ናቸው ብሏል፡፡
የድንገተኛ ሕክምና በተሟላ መልኩ ለማቅረብ ቁልፍ ሚና የቡድኑ አካል የሆኑት የሰመመን ሰጪ ነርሶች መሆናቸውን ያስታወሰው ሰነዱ የእነዚህን ባለሙያዎች ተደራሽነት ለማስፋት በአሁኑ ሰዓት በስምንት የጦና ኮሌጆች 158 ባለሙያዎች በመሰልጠን ላይ ይገኛሉ ሲል ያትታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በጤናው ዘርፍ ያለውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ በብቃት በሰለጠነ የሰው ኃይልና ቁሳቁስ ባልተደራጁት፣እምብዛም ልምድና ክህሎት በሌላቸው አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በገፍ ማሰልጠን መጀመሩና መንግስትም ይህንን በከፍተኛ ደረጃ ማበረታታቱ በዘርፉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ቀጣይነት ባለው መልኩ በመጉዳት መዳን የሚችሉ ወገኖች ጥራት ባለው የሕክምና እጦት ምክንያት ሊሞቱ ይችላል በሚሉ ተቆርቋሪ ወገኖች ከፍተኛ ትችት እየደረሰበት ይገኛል፡፡
በርካታ ሀኪሞች ከአስተዳደር በደልና ከክፍያ ማነስ የተነሳ ስራቸውን እየለቀቁ ወደ ውጭ እንደሚሄዱ ይታወቃል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar