torsdag 16. mai 2013

አጀንዳን እያስቀደሙ ማዘናጋት ከተጠያቂነት አያድንም!


አጀንዳን እያስቀደሙ ማዘናጋት ከተጠያቂነት አያድንም!

አልፎ አልፎ የጉዞን ጎዳና መመርመር ከብዙ ስህተት ያድናል። ግምገማ -እንደሚሉት የ”ለምን አልታዘዝክም” -“ለምን የብዝበዛው አካል/አፋኝ አልሆነክም” ውጠራ ሳይሆን የሕዝቡን የእርምጃ መስመር በተቻለ ለመጠበቅ- ከላስፈላጊ—–ፍጆታም ለመላቀቅ የሚበጅ መሆኑን በማጤን ነው።
በቀደመ መጣጥፍ ስርአቱ አሁን ሞቷል የሚንቀሳቀሰው በበበድኑ ነው የሚል ታማኒ የሆነ ሓሳቦች ተጨብጦ ነበር። ስርአቱ በቁሙ ሙት ነው ግን ዘለቀ ስንል ሊያዘልቁት ያበቁትን ጥቂት ነጥቦች በጥቅሉ ተቀምጠውም ነበር።
አንድ ሀቅ ይፋ መውጣት አለበት ከተባለ መነገር ያለበት አብይ ጉዳይ-የሆነውስ ሆነ- ትላትናና ዛሬ የህዝቡን ትግል የሚመራው ማነ ነበር-ዛሬስ ማነው ብለን መጠየቅ የግድ ነው። እንደ አነጋገርም ስልት “እርሱ አጀንዳ አለው” “የአንተ አጀንዳ ምንድር ነው” “እርሱ የሚያራምደው የራሱን አጀንዳ ነው” ይባላል። በእርግጥም የዚህ ጥቆማ አጀንዳ “አጀንዳ” እንደመሆኑ ሁሉም የራሱ አጀንዳ አለው። የሚያራምደውም አጀንዳውን ነው። የራስን አጀንዳ የሁሉ ማድረግ ደግሞ በክፉም በደጉም አንድ እርምጃ አስቀድሞ ማስተዋልን ያመለክታ።
አጀንዳን አጀንዳ አድርጎ መነሳቱም ትርጉሙ እዚህ ላይ ነው። ብዙ እንደታዘብነውና አሁንም እየተካሔደ እንዳለው የህዝቡን አረማመድ ትግልም ትንቅንቅ የሚመራው ማን ነበር ስንል የምናገኘው ምላሽ በእውነቱ-ባብዘኛው የህዝቡ እንቅስቃሴ ይመራ የነበረው አሁንም የሚመራው የመሰሪው ስርአት እንጂ በሕዝቡ እንዳልነበረ መተማመን መልካም ነው። እድሜ ለእከሌ እንዳንል ሞቷልና የተንኮሉ ምንጭ እንዴት እያንዳንዲቷን እርምጃ በቅጥ እያስተዋለ ሲሸርብ እንደነበረ በቂ ግንዛቤ የወሰደ እዚህ ላይ ግር አይለውም። በመሰረቱ ሕዝብ ወይንም ድርጅቶች አጀንዳ አልነበራቸውም አልተባለም-ተጠለፈ እንጂ-እንቀጥል።
ከየት እንጀምር? ሰለቸን እስከምንል ያሰለቸንን አረማመድ መቃኘት ታሪክ መጻፍ አይነለምና -ይህ ሁሉ ሲሆን የት ነበሩ የሚያሰኝ ሂደት ሆኖ እናገኘዋለን። ትንሽ ትዕግስትን የሚጠይቅ ቁምነገር።
አጀንዳ ስንል አሳቻነቱን፤ጠላፊነቱን፤ሳይቀድሙኝ ልቅደም ባይነቱን፤ ጩኸቴን ቀሙኝነቱን፤መሰሪነቱን ብልጣብልጥነቱን ምን የማይባል አለ -የሚደረደረው የጨለማ አስተሳሰብ ሁሉ እውን የሚሆንበት አረማመዱን ለመጠቆም ነው። ትንሽ ወደሗላ መለስ ብለን የተቻለንን እንናዘዥ-ወይ ፍርጃ!በቁም ኑዛዜ! እስኪ እንደወረደ እንበል።
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት(ባጭሩ አራት አመታት)
የሕዝብ ትግል በጠነከረበት-በቅርብ ለሚያስታውሰው- ስርአቱ የሁለት ባላንጣዎችን ውክልናና ሀላፊነትን ይዞ ሕዝብን በሚሞግትበት ወቅት የኢትዮ-ኤርትራ የእልቂት ጦርነት ሲከሰት ሕዝብን በብሔራዊ ስሜት አንቆ አገር አድን አጀንዳ ተሰመረለት። በዚህ ጊዜ “ከባደሜ መለስ ወደመለስ” -በቀላሉ ይችን ጦርንተ ጨርሰን አናንቀዋለን ተባለ። ሁሉም በተቀየሰለት ቦይ መፍሰስ ጀመረ። እዚህ ላይ ብዙ አርቆ አስተዋዮች-የማያዋጣ-የትግልን ስልት አጨናጋፊ”አጀንዳ” ለመሆኑ አበክረው ቢመክሩም አፈ ጮሌው ባገር ክህደት ከመወንጀል አልተቆጠበም ነበር። የአሰብንም ጉዳይ ያነሱ “ጦረኞች—“ ተባሉ-ለራሳቸውም መከፋፈል መሰረትን ጣሉ-ስንተ አመት?-ባጭሩ አረት አመታት ተሸመቱ። ሕዝብም አለቀ። ከወንጀልም ነጻ!!ያልጄርስን ውዝግብና የህዝብን “ድል አደረግን ሰልፍ ውጡን” ማሞኘት ጨምሮ።
ምርጫ-(ሶስት አማተት ከፊት -አራት አማታት ከሗላ)
ይህ በእንደዚህ እንዳለ ነብረ የ2005 ምርጫ አጀንዳ ሆኖ ሶስት አመት ከምርጫው በፊቱ -ሁለት አመት ከሁዋለው ሲያራኩት የከረመው። ባናሳው አምስት አመት። ከምርጫው ሶስት አመት አስቀድሞ፤ የምርጫ ቦርድን፤ ደንብና ህግን፤የሚዲያ አከፋፋልን፤ታዛቢ ወዘተ ወዘት፤ ምርጫ እንግባ አንገባም ሲባል ካለ በቂ ዝግጅትና የሁሉንም ፈቃደኝነት ባላካተተ መልኩ ወደ ምርጫ ዘው ተባለ። በጦርነቱ አንድ ሆነን ነበር እስኪ ተንፍሱ አይነት በተገኘችው ቀዳዳ የሕዝብ ድል ሲጠናቀቅ፤ በማግስቱ አሸንፌአለሁ ብሎ አውጆ ከዚየም ምድር ቀውጢ እንደሆነች አናስታውሳለን።
ነገሮች ተደማምረው አሁንም የሕዝቡ ድምጽ ይከበር በሚል አጀንዳ በተነሳ ውዝግብ ፤አስቀድሞም ሕዝብ እንዳለቀ፤ወደስር እንደተጓዘ ስናስብ አጀንዳዎችም መልክ እየቀየሩ አንደመጡ እናስተውላለን። ፓርላማ ለመግባት ቅድመ ሁኔታዎች ወዘተ። እዚህ ላይ ከሕዝቡ ድምጽ ይከበር ወደ ገዳዮቹ ለፍርደ ይቅረቡ ከዚያም የታሰሩት ይፈቱ የሚሉት ሁሉ በስርአቱ መሰሪነት የቀረቡ በየወቅቱ የሚፈለፈሉ የግፊት አጃንዳዎች እንጂ ሕዝቡ አስቦ ያቀዳቸው ጉዞዎች አልነበሩም። በቀላሉ አጀንዳዎች ተሰመሩለት።
የታሰሩት ይፈቱ-(አራት አመታት ሙግተ 2+2)
ይህ በዚህ እንዳለ አንድ ጊዜ ከታች ሕዝቡን ሁሉ እስር ቤት ለማስገባት ሞክሮ አንዳላዋጣው ሲረዳ፤ያሰረውን አስሮ አመራሩን በ አጠቃላይ ወደ እስር ሲከት ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ ተረስተው አገር ድፍን-አገር፤ ውስጥ ውጭ “የታሰሩት ይፈቱ” በሚል ሁለት አመት በላይ ሕዝብን በሙግት አጀንዳ ጸና። ምርጫው ተረሳ፤ድምጽ ተሰረቀ፤የተገኙትም ድምጾች ተነጠቁ፤ ነፍሰገዳይ በነጻነት ናኘ። አጀንዳ ተቀየረ።
የቅንጅት አመራርና ሕዝብ እስርቤት ባሉበት ጊዜ ነበር ድርጅቶችን መከፋፈል፤ ወደራሱ ማስጠጋት(ክሎኒንገ)አፋኝ ሕጎችን ማውጣት የተረፉትንም ድርጅቶች እንዳይነቀሳቀሱ ጠፍሮ የያዘበት ሁኔታ የተፈጠረው። የራሱንም ወንጀል አሳልፎ -ባገር ክህደትና -በዘር ማጥፋት ወንጀል ወዘተ አመራሩን ሌሎችንም ወነጀለ። ጩከቴን ቀሙኝ!-አሁን ማን አገርን እንደከዳ ማን ዘር እንዳጠፋ ሐቁ ገሀድ ሊወጣ!!
በጊዜው አጀንዳ ባጀንዳ እየለዋወጠ -ሲፈልገው ፍንጂ አፈንድቶ በማጯጯህ ሲያሰኘውም የፈጠራ ወሬውን እየደለቀ ለ2010 ምርጫ ከበቂ በላይ ዝግጅቱን አጠናቀቀ። በ2005 ስለ 2010 ምርጫ ማሰብ ወንጀል ነበር ማለት ማጋነን አይሆንም። የሶሟያ ጦርነት(ሁለት አመታት)
ድምጽ ሰረቆ፤ሕዝብን አፍኖ፤በቅንጅት አመራርና በሕዝብ መታሰር አገራቀፍና አለመቀፍ ውግዘት የተከናነበው የተንኮለ ስርአት በዚህ ወቅት ያደረገውና መዘንጋት የሌለበት ትልቅ ሸፍጥ-ቀልጠፍ ብሎ ከምእራቡና ተሰላፊዎቹ በበለጠ ግንባር ቀደም ሆኖ ሽብርተኝነትን እንዋጋለን ብሎ ወደ ሶማሌ መዝመቱ ነበረ። የሶማሊያም ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ሆነ! አንደገናም የብሔርን ስሜት ሊቀሰቅስ ሊያሰልፍም ሞከረ፤ሕዝቡ ተምሯልና ልጆቹም በእስር ላይ ናቸውና አልተሳካም። አላማና ውጤቱ ሲጤኑ-አላማው የታሰሩት እንዲረሱ ማዘናጋት ውጤቱ እልቂትና ውርደት ነበሩ። የገባበትን የወጣበትንም ታዝበላልና!። አገርን ካደጋ መከላከል ሌላ ወረራ ሌላ። የአገር ጉዳይ ሌላ፤ የሌሎችን ጥቅም በሕዝብ ልጆች ደም ማስከበር ሌላ። በወቅቱም የታሰሩት ለጊዜውም ቢሁን ተረሱ-ሁለት አመታትመ ተሰቃዩ። በሕዝብ ትግል ቢፈቱም የተነሱበትን አላመ አዳፍኖ ጥያቄው የህልውናና ከስር የመጀመር ጉዳየ ሆነ። እንደለመደው -በጎን ለሚቀጥለው እርምጃው ማውጠንተን መሸረቡን ቀጠለ።
በዚህ ወቅት ነበረ እህት ብርትኳንን ወደ እስር የሰደደዳት-ተከታይ አጀንዳ ይበሉ። ወ/ሮ ብርተኳንን ለማስፈታት እንዲሁ ሌላ ሙግት፤ እርሷን አፈነ፤ምርጫውም ደረሰ- እንደ ጩሉሌ ነጥቆ 99.6% ድል ተነገረ። ቤት ስራውን ጠንቅቆ በተገቢ ሠርቷል። ከስህተቱ ተማረ አምስ አመት ባፈና ደከመ፤ድሉን ነጠቀ አደባባይም ተደሰኮረ። አይን ያወጣ ፍጹም ለታሪክ ለተውልድ ለትዝብት የሚያበቃ ጭፍን ይሉኝታቢስ መሰሪነት።
ዘግይቶም ድርቅ ተከሰተ ብዙ ሙግት። በዚህም ህዝብን ለማትረፍ በሚደረገው ጥረት ዋና የተባሉ የሕዝብ የትግል መስመሮች ደብዝዘው ድርግቶች ታፍነው ተዳክመው- ደርግ ተቃዋሚዎቹን ጸት እንዳሰኘ -ለዚህም መሰሪ ስርአት አፈናው ሰራለት ትንሽ ተንፈስ አለ የተረፉትን ተቃዋሚዎች መለቃቀም ጀመረ።
ምንም የማያልቅበት ተንኮለኛ-ለስሙ መጠሪያ ግድብ ብሎ ተናሰ። ግድብ ሌላ አጀንዳ። ስንት አመት አለፈ በግድብ ሙግት። የሕዝቡ ልጆች ጸረ-ልማት የሆኑ ይመስል ካለአቅም በተጀመረው አወዛጋቢ የግድብ ስራ ብዙ ውጣውረድ ተነሳ፤ እስከ ውጭም ጎዳዩ ተዛምቶ የገንዘብ ቃርሚያው ተቃውሞ በዝቶበት አሁን ባለበት አለ።
ሞተ አለ፤
ሰውየው ታመመ-ሌላ አጀንዳ። ሞተ አለ ብዙ ወራት ተወራ፤ ይቀበር አይቀበር ብዙ ወራት፤ሙዝየም-ሙዚሊየም ነው ምንድር ነው ይገባል አይገባል አሁንም ሌላ ሌላ የሙግት አጀንዳ ——ፍጆታ።
የስልጣን ክፍፍል ሙግት፤
ትንሽ ቆይቶ የሰውየው እሬሳ ሳይደርቅ የስልጣን ክፍፍል ሙግት-አዲስ አጀንዳ። አዲሱ ሰው መጣ፤ አዲስ መነጋገሪያ ሆነ። ሰውየውም በስርአቱ ተጠፍሮ ለውጥ የውሀ ሽታ ብቻ ሳይሆን አራሱ የ“ራኢአይ/ቅዠት” አራማጅ ተብሉ ተኮፈሰ።
ይህ በዚህ እንዳላ ነበር ቀደም ብሎም ስርአቱን እንደ ግለሰብም እንደሺህም ሆነው ለመብት ለነጻነት ቆመው ሲታገሉ የነበሩት አነ እስክንድር–አንዱአለም ወዘተ-የታፈኑት የቀሩት ሸሹ-ሌላ አጀንዳ። አኔም አጃንዳ ማለቱ ደከመኝ፤አሰልቺ ነው። ከአንድ ወጥመድ ወደሌላ ወጥመድ ካንድ አዘቅት ወደ ሌላ አዘቅት-በተለያየ መለኩ። አሁንም ካለፈ ልምዱ -ብዙም መነጋገሪያና ተስፋ ሰጭም ባይሆን -የክልል ምርጫ ተባለ እንደተለመደው ተጠለፈ። ሐይማኖትንም በሚመለከት-ያመራሩንና ገዳማትነ አያይዞ ለብዙ ጊዛ ውጣውርደ እስካሁን እየቀጠለ ያለ መሆኑን ስንመለከት-ሌላው አነጋጋሪ የሐይማኖት ሙግት አጀንዳ እንደሆነ መጣዘብ መልካም ነው።
የሕዝብ ማፈናቀል፤
የሰውየውን ማጣጣር-ሞት አመላክቶ የሕዝቡ መነሳሳት ግልጽ በሆነበት ወቅት፤አደገኛ አካሄድ ቢሆንም -ለጊዜውም ሕዝብን በማንጫቻት የሰራላቸው አንድ አስከፊ ነገር ተከሰተ። ባገሪቱ አደገኛ አዝማሚያን የቀሰቀሰ ከሶስቱም ማእዘናት ሕዝብ ማፈናቀል። ሌላ መዘዘኛ አጀንዳ። በሔደቱም አዲሱ ሰው እግሩን ተከለ የመሰለውን መስሎ ወጣ። የመረጋጋት ስሜትን የፈጠሩ መሰላቸው ነገር ግን ምን ምሰው እንዳወጡ በቅጡ የተረዱት አይመስልም። በዚህም እስከዛሬ ሲያራምዱት የቆዩት የዘረኝነት ደባ ገሃድ ወጣ። አራስን የሚለበልብ አጀንዳ። ሟች ይህን እንዴት እንዳመለጠ ትዝብት ይወሰድ። ጭልጥ ያለች ውሸትን እወነት አድርጎ መናገር ይችልበት ነበር። በዚህም ከዚህ የቀደመውም የሕዝብ መሰረታዊ ጉዳይ ሁሉ ተረሳ።
ሙስና፤
አሁን ደግሞ የተያዘው አጀንዳ ሙስና ሆኗል። ሟቹ- የስርአቱ አማራማጆች በሙስና የተዘፈቁ መሆናቸውንና ከ50% በላይ ስለሆኑ መዋጋቱ አንደማያዋጣው ስለተረዳ -አልፎም ስርአቱ የቆመበትን ምሰሶ የሚያናጋ በመሆኑ ሳይነከው ተሰናበተ። የብልጠት አረማማድ ነበረ። የሚያዋጣውንና የማያዋታውን ያውቃል። አዲሱ ሰው ምን ውስጥ ተዘፈቀ? ሙስና የስርአቱ ስም እንጂ የአንድ ግለሰብ ወይንም የተወሰነ ባለስልጣን መስሪያቤት ችግር ብቻ አይደልም። ከሙስና ለመጽዳት ወይ 50ዎቹን ስርአቱ ይጨርስና ለሕዝቡ የቀረውን ይሰጥ ወይም ይሰናበቱ። እዚህ ላይ ምን ተረሳ -የሕዝብ መፈናቀል። ጥሩ ሙከራ።
ይህን ስርአት ከሙስና አጸዳለሁ ማለት ዘበት ከዘበትም ዘበት ነው-አያችሁ አጀንዳ -በል በል የሚያሰኝ፤ አጀንዳ ማለት ይህች ነች።በተግባር።
ይሀን ሁሉ ሲያደርግ ሶስት አነኳር ቁም ነገሮች መጠቀስ አለባቸው። ለዚህ ሁሉ -አላማው ግልጽ ነው፦
1. ማዘናጋት-አላማን ማሳት፤
2. ከተጠያቂነት ማምለጥ-በእያንዳንዱ አጀንዳን መቀያየር ከስንት ወንጀልና ተጠያቂነት እንዳመለጠ ግልጽ ነው፤
3. ተቃዋሚን /ሕዝብን ማዳከም፤
4. ፈጥኖ ጥቅምን ማግበስበስ፤
5. ብሎም የስልጣን እድሜን ማራዘም። ከሆነው ሁሉ፤የቱ እንተሳካለትና የቱ እንደከሸፈበት አንባቢው ይፍረድ።
እንዲህ እንዲህ ሲል ነበር 22 አመታት ሕዝብን ሲሞገግት ሲመሰጥር ሲያምስ የከረመው። መቃወምም አጀንዳ ሆነ- ሁሉም የታየውን ዘርዘር አድርጎ ማስቀመጥ ሀላፊነት አለበት- በዚህ ረገድም ብዙ ተብሏል። ባንድ መልኩ የስርአቱ ምንነት የተረጋገጠው ይህን ንቅዘቱን በማጋለጥ ረገድም ነበር፡
ለማጠቃለል ከዚህ ምን እንማራለን? በዚህችው በመጨረሻ የእስትንፋስ ጊዜው፦
1. የ ስርአቱን አዘናጊ አጀንዳ ጠንቅቆ መረዳት፤
2. ይህ ያንተ አጀንዳ እንጂ የሕዝቡ አይደለም ማለት፤ አለማጀብ፤በመንገዱም አለመሔድ፤ማምከን፤
3. ትኩረት ባለው የሕዝብ አጀንዳ ላይ መንቃሰቀስ፤
4. የህዝብን የመሰረታዊ የዲሞከራሲ፤የነጻነት፡የመብት ጥአቄዎችን፤የአገርን ሉአላዊነት አንድነትና ዘላቂነት የሚመለከቱትን ጉዳዮች በማጉላት-የለውጥን ባቡር ጉዞ ማፋጠን።
ከዚህ -ከምናውቀው ከተማርነውና ካስተዋልነው አንድ ተጨማሪ ግንዘቤ እንደወሰድን ይገመታል። በዚህም የስርአቱን የወደፊት አጀንዳ አስቀድም መተንበይ ይቻላል። በሚገርም ሁኔታ የ2015 ምርጫን አንስተው ሕዝን ሊያንጫጩ እንደሚሞክሩ መገመት አያዳግትም። አንድ ታምር -እንበለውና- አንድ ነገር ካልመጣ ስርአቱ እንዲሁ በድኑን እየተንቃሰቀሰ፤ ሙቱን አየተንገዳገደ፤ አደጋ አያንዣበበበት እዚያ ሊደርስ አንደሚሞክር መገመት አያዳግትም። ለነገሩ መሰሪነት ጨርሳ ባትጠፋም ሳትሞት አልቀረችም። ለእነርሱም ሰዎች -ጊዜአቸው
አስቀድሞ ያበቃ፤ በተዋሰ ጌዜ እንደሚንቀሳቀሱ፤ ጊዜና ሕዝብ እንደከዳቸው ሀይልም ትምክህትም ሸፍጥም አንደማያዋጣ ቢረዱና መንገዳቸውን ቢፈልጉ ከባሰ ሁለገብ ቀውስ መዳን ይሆናል ።
ይህም ሆኖ በየወቅቱ አዘናጊና አደናቃፉ አጀንዳዎች ቢደቀኑበትም -ሕዝቡ እንደተባለውም፦
በሰራው ወጨፎ በሰራው እርሳስ፤
ጥልያን ጠፈጠመ ዳግመኛ እንዳይደርስ!
ብሎ በገዛ አጀንዳው እተመታና እፍረትን ውርደትን እየተከናነበ እዚህ የድል ምእራፍ ላይ እንደደረሰ መጠቀስ አለበት። ሕዝቡ ምንጊዜም ባለድን ነው። ሕዝብን ዘለአለም ለማታለል መሞከርና -ለጊዜውም ቢሆን- ተላላነት ነው።
ለማጠቃለል-የኤርትራ ጦርንተ ተባለ ትረፉ እልቂት፤ውርደት። የአልጄርስ ስምምነት ድለ ነሳን ተባለ ባዶ ኳካታ ውርደት። ምረጫ ተባለ ሽንፈት። ወደእስር በሐሰት ክስ የገቡትመም ተፈቱ–ውርደት። የሶማሌ ጦርነትም ትረፉ እልቂት-ያለቀው ቁጠሩ እነኳ ሳይነገር-አሊ-ሽባውም አግር አውጠቶ ተጠናከሮ ጦርነቱን ቀጠለ። ድርቅ ተከሰተ-ድርቅና ረሃብ የቋንቋ አቃቂር መጣ-አንድም ሰው አልሞተም-ተባለ በቅርቡ በሶማሊያ ከ260፣000 ሕዝብ በላይ ማለቁን ተነገረ። አሁንም የምስራቁ ኢትዮጵያ ጉድ ተዳፍኖ አለ-ትልቅ መጪ ውርደት። ዳግም ምርጫ ተባለ-99.6% ውርደት። ሰውየው በሕይወት አለ ሲባል ተከረመ-ሰውየውም ሞተ። የሕዝብ ማፈናቀል ተሸረበ-የባሰ ውርደት የዘረኝነት ሴራ መጋለጥ። አሁን ደግሞ ሙስና ተባለ-ሲወተወት የነበረው የስርአቱ በዝርፊያ መንቀዝ በራሱ ኮሚሽን ይፋ መውጣት የባሰ ዝቅተት። ብዙ ሊጻፍ ሊነገር ይቻላል። ሕዝቡ ስርአቱን በአጀንዳው ካጠናቀቀው፤በራሱ አጀንዳ ቢራመድ ምንኛ የመከራው ጊዜ ባጠረች። ይህም ሲባል በሕዝቡ አጀንዳ ላይ ሳያሰልሱ ሲታገሉ በመጨረሻም የተናገሩት እውነት መሆሉን በተግባር በብቃት ያስመሰከሩ ብዙዎች እንዳሉ መጠቀስ አለበት።
ለቀባሪው አረዱት አይሁንና-ቁምነገሩ ሕዝቡ በስርአቱ አጀንዳ ሳይሆን በራስ አጀንዳ ስር መንቃሰቀስ አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን ማመልከት ተገቢ ነው። ስርአቱ ከእንግዲሕ የቀረው የቅዠት አጃንዳ ብቻ ነው። በዚህ መሄድ ደገሞ -በሌላው ቅዠት መቃዠት ነው የሚሆነው! ከእንግዲህም ቀልጠፍ ብሎ -አጀንዳህ ምድረ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል። አግባብነት ያለው ተመራጭ አጀንዳ-የተባበረ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ነው ቢባል ተገቢ ይሆናል! አጀንዳዎችን አጥንቶ መጓዝ ተገቢ ነውና!! እንቅስቃሴውም -ሲፈለግ የነበረውን አንድነት ቅንጅትና ሕብረት ሊያመጣ ይችላል።አንድነት ለእንቅስቃሴ፤እንቅስቃሴም ለአንድነት።
አጀንዳን እያስቀደሙ ማዘናጋት ከተጠያቂነት አያድንም!!!
ኢትዮጵያ በእግዚአብሔርና በጠንካራ ታጋሽ በሕዝቧ ተጠብቃ ትኑር!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar