onsdag 19. juni 2013

የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተጠየቀ

የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተጠየቀ

የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተጠየቀ


ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ የተለየና የዓመት በዓል ዋዜማ የሚመስል ድባብ የታየባቸው አካባቢዎች ነበሩ፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም ድባብ ደግሞ እጅግ የተለየ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በማግስቱ የሚያደርገው ጨዋታ አልደርስ ያላቸው እግር ኳስ ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ በስታዲየም ዙሪያ ማንዣበብ የጀመሩት ቅዳሜ ከቀትር ጀምሮ ነበር፡፡
ከሰዓት በኋላ ደግሞ ወደ ስታዲየም የሚያስገባውን ትኬት ለማግኘት ሠልፍ ለመጀመር የሞከሩም ነበሩ፡፡ 
በዋዜማው የብሔራዊ ቡድኑን ድል በመተንበይ በሚመስል ሁኔታ የተጨፈረባቸው መዝናኛ ቤቶችም እንደነበሩ ተረጋግጧል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር ያደረገው ጨዋታ የተጠበቀው በታላቅ ጉጉትና በጭንቀትም ጭምር ነበር፡፡ 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማሸነፉን የሚያበስረው የዳኛው ፊሽካ ድምፅ መሰማቱን ተከትሎ፣ በስታዲየም የታየው ሁኔታ እንዲህና እንዲያ ተብሎ በቃላት የሚገለጽ አልነበረም፡፡ ብዙዎች በሲቃ አንብተዋል፤ ጮኸዋል፤ ዝለዋል፡፡ ይህ በስታዲየም ብቻ ሳይሆን፣ በመላው አዲስ አበባና በክልል የተለያዩ ከተሞችም የቡድኑን ድል ተከትሎ የታየው ጥልቅ ደስታ ቅንጭብ ነፀብራቅ ነው፡፡
አዲስ አበባ ማምሻዋን በጭፈራና በሆይታ ደምቃ አመሸች፤ አደረች፡፡ ደስታው የሚያልቅ ወይም የሚደበዝዝ አይመስልም ነበር፡፡ አዛውንት፣ ወጣት፣ ሕፃን፣ ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሐሴት ተሞልቶ አመሸ፤ አደረ፡፡ እሑድ ምሽት ላይ ግን ይህን ታላቅ ደስታ የሚያደበዝዝ ዜና ተሰማ፡፡ ሁለት ቢጫ ካርድ የተመለከተ ተጫዋችን የኢትዮጵያ ቡድን ከቦትስዋና ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ማሰለፉ ጥፋት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ እንደምትቀጣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ማሳወቁን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኅን ዘገቡ፡፡
ይህ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ጥፋቱ የማን ነው? ኃላፊነቱንስ የሚወስደው ማን ነው? የሚሉና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች በብዙዎች ተነሱ፡፡ ዋናው ጉዳይ ደግሞ የቡድኑ ቀጣይ ዕጣ ምን ይሆናል? የሚለው ሆነ፡፡ በዚህ ዙሪያ ሁሉም በየፊናው ተወያየ፣ ተጨነቀም፣ ይበልጥ ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑን ውጤት ተከትሎ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ደስታቸውን በመግለጽ ላይ የነበሩ ወጣቶች ሕልፈተ ሕይወት በተለያዩ መገናኛ ብዙኅን መሰማቱ አሳዛኝ ክስተት ሆነ፡፡ 
የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ብቻ ሳይሆን፣ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ጭምር አስተያየቶች፣ ጥቆማዎችና ጠንካራ ትችቶች መስተጋባቸውም አልቀረም፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ማክሰኞ በግዮን ሆቴል በሰጡት መግለጫ በተፈጠረው ስህተት ክፉኛ ማዘናቸውን በመግለጽ፣ ለተፈጠረው ችግርም ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ተናግረው፣ ለጥፋቱ ተጠያቂ ያደረጓቸውን አመራሮችና ሠራተኞችን ይፋ አድርገዋል፡፡ 
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ለተፈጠረው ችግር ማብራሪያ ከመስጠታቸው አስቀድሞ፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የተፈጠረውን ችግር ያሳወቃቸው እሑድ በአዲስ አበባ ስታዲየም የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ ጨዋታ ከመደረጉ አስቀድሞ ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. መሆኑን፣ ነገር ግን ጉዳዩን የተወሰኑ የፌዴሬሽን አመራሮች ብቻ እንዲያውቁት ተደርጐ እንደቆየ ተናገሩ፡፡ 
እሳቸው እንደሚሉት፣ ያንን ያደረጉበት ምክንያት መረጃው ይፋ ከሆነ በእሑድ ጨዋታ ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ በማያያዝም ቡድኑ እሑድ ዕለት ያስመዘገበው ውጤት የተጫዋቾቹን፣ የሕዝቡን፣ የፌዴሬሽኑን፣ የሠራተኞቹንና የአሠልጣኞችን የተቀናጀ ሥራ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 
አቶ ሳህሉ ሲቀጥሉ፣ ባለፈው ሰኞ ከቀኑ አሥር ሰዓት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ መገማገም አድርጐ በመጨረሻም የጋራ አቅጣጫ አስቀምጦ ወጣ፡፡ በግምገማው የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አቶ ሰውነት፣ የቀድሞው ረዳታቸው አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ፣ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና ሌሎችም አካላት እንደተካተቱም አስረድተዋል፡፡ 
በግምገማው መሠረት ከፊፋ የመጣው መረጃ ትክክል ነው አይደለም? ከፊፋ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ደንብ ጋር በማገናዘብ ለቅጣቱ ምክንያት ከሆነው ምን ያህል ተሾመ ጀምሮ ሌሎችም በየደረጃው ተሰጧቸው የተባሉ ቀይና ቢጫ ካርዶች እንዴትና ከየትኛው ጨዋታ የሚለው በዝርዝር ታይቶ፣ ‹‹እውነትም ስህተት ፈጽመናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ለፊፋ ይግባኝ የምንጠይቅበት፣ እውነትን የምንሸሽበት ሁኔታ የለም፤›› ሲሉ ጥፋቱ የተረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 
አቶ ሳህሉ ይህን ለመሰለው የተረጋገጠ ጥፋት ተመጣጣኙ ዕርምጃው ምን መሆን አለበት የሚውን ከማብራራት ይልቅ፣ ቀጥለው የተናገሩት ፌዴሬሽኑ ለጥፋቱ ተጠያቂ ብሎ ያመነባቸውን አመራሮችና የፌዴሬሽን ሠራተኞች ማንነት በማጋለጡ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የፊፋን መረጃ መቃወም ከመላላጥ ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው በመግለጽ ለስህተቱ ተጠያቂ የተደረጉት የመጀመርያው ተጠያቂ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ከበደ ናቸው፡፡ 
እሳቸውም በተለይም በእሳቸው የቡድን አመራርነት ለጠፋው ጥፋት ማንንም ተጠያቂ ማድረግ እንደማይፈልጉ ተናግረው፣ ሁኔታውን በተመለከተም ለስህተት ስለዳረጋቸው ክስተት ብዙ መናገር የሚፈልጉት እንዳለ ‹‹ቢሰማኝም›› ብለው፣ ‹‹የምናገረው ለህሊናዬ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ማንንም ለማስደሰት ወይም ለማሳዘን አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ፈርመህበታል የተባልኩት ደብዳቤ ኮፒም ሆነ ዋናው በእጄ የለም፡፡ እንደተሰጠኝ የተነገረኝ ከብዙ ወረቀቶች ጋር እንደሆነ ነው፡፡ ይህንን የምለው ሰዎችን ተጠያቂ ለማድረግ አይደለም፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ሳስበው ነገሩ እንዴትና በምን ሁኔታ እንዳመለጠኝ ጥያቄ ሆኖብኛል፡፡ የቢጫና ቀይ ካርዱን በተመለከተ ግን እነማን መቼና እንዴት እንደተመለከቱ መመዝገቤንም አላቆምኩም፡፡ ነገር ግን ምንያህል ሁለት ቢጫ እንዳለው አሁን ላይ ሆኜ ካልሆነ በምንም መመዘኛ አዕምሮዬ ውስጥ አልነበረም፡፡ የማውቀውም ነገር የለም፡፡ ሌሎች ወረቀቶች እጄ ላይ አሉ፡፡ ስለ ምንያህል ኮሙኒኬ ጉዳይ ከፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ተሰጠህ የተባልኩት ደብዳቤ ግን እጄ ላይ አልነበረም፡፡ በውስጤ የነበረውም የኢምግሬሽን ጉዳይ ነው፡፡ ቡድኑም ተሟልቶ ዝግጅት አለማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የአውሮፕላን ትኬት ችግርም ስለነበረ የማስበው ያንን ነው፡፡ በዚያ ላይ የመሥርያ ቤት ሥራም እንዳለ መዘንጋት የለበትም፡፡ በቃ የምክደው ስህተት አይደለም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ነው ጉዳዩ ብሎ በጽሕፈት ቤትም ሆነ በሌላ አካል ማንም ሰው የነገረኝ የለም፡፡ የመጀመርያህ እንደመሆኑ እዚህ ላይ ተጠንቀቅ ልባል በተገባ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ በዚህም ሰዎችን ተጠያቂ ማድረግ አልፈልግም፤›› ብለዋል፡፡ 
የምክትል ፕሬዚዳንቱን አስተያየት ተከትሎ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ እጅጉ በበኩላቸው፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ከእያንዳንዱ ጨዋታ በኋላ ለአባል ፌዴሬሽኖች እንደሚያሳውቅ ተናግረው፣ በዚያ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመርያውን ጨዋታ ግንቦት 25 ቀን 2004 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ ላይ በተጫወተበት ወቅት ከምንያህል ተሾመ ጀምሮ እነማን ቢጫ ካርድ ስለመመልከታቸው፣ ግንቦት 27 ቀን 2004 ኮሙኒኬውን እንደላከ፣ ከዚያም የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ለሚመለከታቸው አካላት እያስፈረመ እንደሰጠ፣ ይህንኑ በወቅቱ የቡድን መሪ ለነበሩት አቶ አፈወርቅ አየለ እንደተሰጠ፣ ቀጥሎ ቦትስዋና ከኢትዮጵያ ጋር ሲጫወቱ አቶ አፈወርቅ ኃላፊነታቸውን ለአቶ ብርሃኑ ከበደ እንዳስረከቡ፣ በቦትስዋናና በኢትዮጵያ ጨዋታ ላይም ተጫዋች ምንያህል ቢጫ ካርድ እንደተመለከተ፣ ከእሱ ጋር በረኛው ጀማል ጣሰው ጭምር ቢጫ ካርድ መመልከታቸውን አስመልክቶ ፊፋ ጨዋታው በተደረገ በሦስተኛው ቀን መጋቢት 18 ቀን 2005 ዓ.ም. ኮሙኒኬ መላኩንና ያንንም ጽሕፈት ቤቱ ለቡድኑ የቡድን መሪ አቶ ብርሃኑ ከበደ አስፈርሞ እንደሰጠ አሠልጣኙ አቶ ሰውነትም እንደደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ 
በሁለተኛ ደረጃ ተጠያቂ ተደርገው የቀረቡት አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው፣ ውጤቱ እንደህ በቀላሉ ተላልፎ የሚሰጥ እንዳልሆነና ከእሳቸው ጭምር አሠልጣኞችም ሆኑ ራሷ አገሪቷ የተሰደበችበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሲቀጥሉም፣ ‹‹ሥራው አዲስ ታሪክ ሠርተን አደባባይ ወጥተን ልንናገር የተዘጋጀንበት ነው፡፡ ድርጊቱ በመከሰቱ ከልቤ አዝኛለሁ፡፡ ጉዳዩ ከእኔ አምልጧል፡፡ በዋናነት ደግሞ ከባለጉዳዩ ምንያህል አምልጧል፡፡ ከተጫዋቾች በአጠቃላይ አምልጧል፡፡ አንዴ ሆነ የሆነ ነገር ደግሞ አይመለስም፡፡ ከዚህ ውጭ ጽሕፈት ቤቱ ሰጥቼዋለሁ የሚለው ኮሙኒኬ አልደረሰኝም፡፡ በእርግጥ መረጃው አልደረሰኝም ብዬ ዝም ማለት አልነበረብኝም፡፡ መጠየቅም ነበረብኝ፡፡ ተጫዋቹም ሊነግረኝ በተገባ ነበር፡፡ ባልጠበቅነው ሁኔታ የመረጃ ክፍተት ተፈጠረ፤ ሁኔታው ተከሰተ ያሳዝናል፡፡ የሚገርመው ወሬውን የሰማሁት ሰኞ ዕለት ጠዋት ምንያህል ደውሎ ኧረ እንዲህ እየተባለ ነው ብሎ ሲነግረኝ ነው፡፡ ሰነድ እንይዛለን፣ ነገር ግን የእሱ እንዴት እንዳመለጠን ገልጽ አልሆነልኝም፡፡ አሁን ምን ይሁን? ሦስት ነጥብ ለቦትስዋና ተሰጠ፣ የሚቀርብን ከማዕከላዊ አፍሪካ ጋር ሁለተኛውን ቡድን ለመሞከር የነበረን ዕቅድ ከሽፏል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን አሁንም ምድቡን እየመራን ነው፡፡ በሚገባ ተዘጋጅተን ማዕከላዊ አፍሪካን አሸንፈን ሕዝባችንን እንክሳለን፡፡ ክስተቱ ከስህተታችን ተምረን የአሠራር ሥርዓታችንን አጠናክረን እንድንቀጥል የሚያግዝ ነው፡፡ ኃላፊነቱም እነዚህን ጥቃቅን ነገሮች እናዳናስታውስ አድርጐናል፤›› ብለዋል፡፡ 
ከአቶ ብርሃኑ ከበደና አቶ አሸናፊ፣ እንዲሁም ከአቶ ሰውነት አስተያየት በኋላ ማብራሪያቸውን የቀጠሉት አቶ ሳህሉ፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ አሸናፊ እጅጉ የሰጡት ማብራሪያ በቂ እንዳልሆነና በተለይም ከመረጃ ፍሰት አኳያ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ፣ ካልሰጡ ግን በግምገማው ወቅት የሰጡትን የእምነት ክህደት ቃል እሳቸው እንደሚናገሩ ባሳሰቡት መሠረት አቶ አሸናፊ ፌዴሬሽኑ ጫና እንዳለበት፣ ያም ቢሆን ግን እንደ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መረጃውን ለሚመለከታቸው አካላት እንዳስተላለፉ ደጋግመው አረጋግጠዋል፡፡
በቀጣይ ተጠያቂ የተደረገው ደግሞ ቀደም ሲል በተለይም ደቡብ አፍሪካ ላይ ጨዋታው ሲከናወን የአቶ ሰውነት ረዳት የነበሩት አቶ ሥዩም ከበደ ናቸው፡፡ አቶ ሥዩም ስለሁኔታው ገለጻ ባይሰጡም፣ በአቶ ሳህሉ በኩል እንደተገለጸው ከሆነ፣ በወቅቱ የቡድኑ ምክትል አሠልጣኝ በመሆናቸው ምንያህል ቢጫ ካርድ አይቷል፣ አላየም የሚለው መረጃ እንዳላቸው ያውቃሉ፡፡ ተጫዋቹ ሁለተኛውን ቢጫ ካርድ አዲስ አበባ ላይ ከቦትስዋና ጋር በነበረው ጨዋታም መመልከቱን እሳቸው ረዳት ባይሆኑም ለመረጃ ካላቸው ቅርበት አኳያ ማወቅ ነበረባቸው፡፡ አውቀውም ሁኔታውን ለዋናው አሠልጣኝ፣ አሊያም ለፌዴሬሽኑ መግለጽ ሲገባቸው ዝምታ መምረጣቸው አግባብ አለመሆኑን እንደተገመገሙና ጥፋታቸውንም እንዳመኑ ተናግረዋል፡፡ 
ሌላው ተጠያቂ የተደረጉት የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ አባልና ቀደም ሲል የብሔራዊ ቡድኑ ቡድን መሪ የነበሩት አቶ አፈወርቅ አየለ ናቸው፡፡ የእሳቸውም ጥፋት በተመሳሳይ መንገድ በአቶ ሳህሉ ገብረ ወልድ ተገልጿል፡፡ አቶ አፈወርቅም ጥፋተኛነታቸውንም እንዳመኑ ተናግረዋል፡፡ በተለይ መረጃን ከማስተላለፍ አኳያ ክፉኛ ተወቅሰዋል፡፡ 
ቀጥሎ ጥፋተኛ የተደረገው ምንያህል ተሾመ ነው፡፡ ኃላፊው ተጫዋቹን አስመልክቶ በግምገማው ወቅት እንዲገኝ ተጠርቶ እንዳልተገኘ፣ ይሁንና በሁኔታው ተበሳጭቶ ሞባይሉን አጥፍቶ ቤት ውስጥ ከሰዎች ተገልሎ እንደነበር፣ ዞሮ ዞሮ ግን እንደ ፕሮፌሽናል ተጫዋች በሚዲያ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚኖር ጭምር ተናግረዋል፡፡ 
አቶ ሳህሉ በማስከተልም፣ የኃላፊነትንና የተጠያቂነትን ሥራ በየደረጃው ከፋፍለው ሲሰጡ በተገቢው ሁኔታ ኃላፊነትን መወጣት ባልቻሉ አባሎቻችን እንዝህላልነት ይኼ ሁኔታ በመፈጠሩ እንዳዘኑ፣ ሆኖም በየደረጃው ጥፋተኛ የሆኑ ከአመራሮች ጀምሮ እስከ ሠራተኞች ተገቢውን የዲሲፕሊን ዕርምጃ ወስደው ለሕዝብ እንደሚያሳውቀም ተናግረዋል፡፡ 
ኅብረተሰቡና ጋዜጠኞች ምን አሉ?
ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ትልቅ መነጋገሪያ እንደሆነ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማክሰኞ ጉዳዩን አስመልክቶ በይፋ ጋዜጣዊ መግለጫ እስከመስጠት ድረስ ለዝግጅት ክፍላችን ከየአቅጣጫው የሚደርስን ጥቆማ፣ ‹‹በብሔራዊ ቡድናችን ውጤት የተሰማንን ደስታ ሳናጣጥም በፌዴሬሽኑ አመራሮች ድክመት በተፈጠረ ችግር ደስታችን በሐዘን እንዲለወጥ በመደረጉ እናዝናለን፡፡ ይሁንና አንድ ተስፋ አለን፡፡ የፊፋን ውሳኔ ማስለወጥ ባይቻልም ለዚህ የዳረጉንን የፌዴሬሽን አመራሮች ተጠያቂ መደረግ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አንዳንዶች ከሚዲያው ጀምሮ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ መደረግ እንዳለባቸው ነው፣ ነገር ግን ይኼ ብቻውን በቂ አይደለም፣ ተጠያቂም መደረግ አለባቸው፤›› የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የበርካቶች ጥያቄ አመራሮቹ ዛሬ ነገ ሳይሉ ይውረዱ ነው፡፡ 
ማክሰኞ ፌዴሬሽኑ ስለጉዳዩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከወትሮው በተለየ በርካታ የመገናኛ ብዙኅን ሙያተኞች ተገኝተዋል፡፡ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በኢትዮጵያ ቡድን ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ያቀረቡት ጥያቄ በዋናነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዚህ ጥፋት ግለሰቦችን ለይቶ በማውጣት ተጠያቂ ማድረግ እንደማይገባው፣ መጠየቅም ካለበት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ሁሉም ሊሆኑ እንደማገባ ተንፀባርቋል፡፡ 
ከጥያቄዎቹ በርካቶቹ ደግሞ በሌሎች አገሮች የእዚህ ተመሳሳይና በተለይ ሕዝብን የሚያሳዝኑ ጉዳዮች ሲፈጠሩ አመራሮች ከምክንያት በፊት የሥራ መልቀቂያ እንደሚጠይቁ በመጥቀስ፣ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ምክንያት ከመደርደር ይልቅ ማድረግ የሚገባቸው በገዛ ፈቃዳቸው የአመራርነቱን ቦታ ማስረከብ የሚለውን አንፀባርቀዋል፡፡ 
ሌላው ፌዴሬሽኑን ለእዚህ ዓይነቱ ውድቀት የዳረገው በሚከተለው ኋላቀር አሠራር እንደሆነና ይህን እስካልቀየረ ድረስ ደግሞ ማንም ሰው ወደ ፌዴሬሽኑ ቢመጣ ለውጥ እንደማያመጣ፣ የሚፈጠሩት የአሠራር ብልሽቶች ሁሉም ተቋሙ የሚከተለው የአሠራር ሥርዓት የወለዳቸው በመሆናቸው፣ በዘመኑ የአሠራር ሥርዓት መቀየር እስካልቻሉ ድረስ ከዚህ የባሰ አሳፋሪ ድርጊት መቀጠሉ እንደማይቀር ጥያቄያዊ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ ማጠቃለያዎቹ ግን የፌዴሬሽኑ አመራሮች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኃላፊነታቸው መልቀቅ እንደሚገባቸው ነው፡፡
የፌዴሬሽኑ አመራሮች መልስ
ከጋዜጠኞች ለቀረቡት ጥያቄዎች የመጀመርያውን ማብራሪያ የሰጡት የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ ሲሆኑ፣ ‹‹እጅግ በጣም ወሳኝና አሳዛኝ ክስተት ላይ ተገናኝተን መነጋገራችን እንደ ሥራ አስፈጻሚ አዝኛለሁ፡፡ በቀጥታ እኔን የሚመለከት ጥያቄ ባይኖርም፣ ነገር ግን በፌዴሬሽኑ ውስጥ የሥራ ክፍፍል አለን፡፡ ይህም ለእግር ኳሱ ዕድገት ሲባል የተደረገ የኃላፊነት ድርሻ ነው፡፡ እንደ ተቋም ለሚፈጠሩ ስህተቶች ተጠያቂነቱም የጋራ ነው፡፡ በግል እያንዳንዱ በተሰጠው የኃላፊነት ድርሻም ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባ ግን አምናለሁ፡፡ ይህን የምለው ችግሩን ወደ ሰዎች ለመወርወርም አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ግን እንዳተባለው ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የሆነ የሲስተም ችግር አለበት፡፡ ውስብስብ ችግርም ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ በአሁኑ ወቅት በእግር ኳሱ ለውጥ የለም ማለት አይደለም፡፡ ስህተት የሥራ ውጤት ነው፡፡ ስህተቱ ግን ትልቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሥራ ባንሠራ ስህተቱ አይመጣም ነበር፡፡ በእርግጥ የዕውቀት ክፍተትም ስላለ በሽግግር ላይ እንድንሆን አስገድደናል፡፡ ስለዚህ የተፈጠረው ስህተት ሥራ ያመጣው ነው፡፡ በሌሎችም አገሮች ይፈጠራል፡፡ ይህን ስንል ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ አንጠይቅም ማለት አይደለም፡፡ በትልቁ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ ከዚህ ውጭ ምርጫና ተያያዥ ነገሮች ላይ ለተነሳው ጥያቄ የሚሠራው የተወከለ ሰው ነው፡፡ ብቁ ነህ፣ ታገለግላለህ ከተባልኩ ላገለግል ዝግጁ ነኝ፣ አትችልም ከተባልኩም እንደዚያው፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው በበኩላቸው፣ እንደሚስተዋለው የሁሉም ጥያቄ አንድ ነገር ላይ ያተኮረ ስለመሆኑ ሲያብራሩ፣ ‹‹በተፈጠረው ስህተት ፌዴሬሽኑ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት የሚል ነው፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን ደግሞ የአመራርነቱንም ቦታ መልቀቅ አለባችሁም እየተባለ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑና አመራሩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው፡፡ ስለዚህ ኃላፊነት ወስደን ተጠያቂነትንም የምንሸሽበት ሁኔታ የለም፡፡ ያለው አመራር በጋራ አመራር ነው፡፡ ኃላፊነቱንም በጋራ እንወስዳለን፡፡ አቶ ሳህሉ መጀመርያም እንደተናገሩት፣ ‹‹ጥፋት ፈጽመናል ነው ያሉት›› ስለዚህ ተጠያቂዎች ነን፡፡ ይህ የሚሆነው እንደተቋም ሲሆን፣ ነገር ግን ጅምላ ሊሆን አይገባም፡፡ ኃላፊነቱን የሚወስዱ በየደረጃው ስለተቀመጡ ማለት ነው፡፡ በእነዚያም ላይ ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡ ሥራ ካለ ስህተት አለ፡፡ በእኛም የተፈጠረው ይኼ ነው፡፡ አጥፊው ተለይቶ ይታወቅ ተባለ፣ በተባለው መሠረት ጥፋተኛውን ለይተናል፡፡ በሕግ አነጋገር ሁለት ዓይነት ጥፋት አለ፡፡ ሆን ተብሎና በቸልተኝነት ናቸው፡፡ ስለዚህ በእኛ ፌዴሬሽን የተፈጠረው ስህተት በቸልተኝነት የተፈጠረ ነው፡፡ ለ12 አምስት ጉዳይ በተፈጠረ ስህተት የሦስት ዓመት ተኩል ልፋት ገደል መግባት አለበት ብለን አናምንም፡፡ እንደ እኔ ግን መጥኔ ለሚቀጥለው፤›› ብለው፣ ‹‹ነገር ግን በፌዴሬሸናችን ውስጥ ዝርክርክ አሠራር አለ፡፡ መስተካከል አለበት እንቀበለዋለን፡፡ ስለዚህ ጽሕፈት ቤታችን የተበላሸ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
አቶ ሳህሉ በበኩላቸው፣ ፌዴሬሽኑን በተቻለ መጠን ከኋላ ቀር አሠራር ወደ ዘመናዊ አሠራር ለማስገባት  እያስተካከሉ መሆኑን ገልጸው፣ አመራሩ ግን ጉልበቱን ሳይቆጥብ መሥራት ያለበትን ሁሉ ሠርቷል፡፡ ‹‹እርግማን ነው መሰለኝ የተሠራን ሥራ ማድነቅ የለም››፣ ያሉት አቶ ሳህሉ፣ በቀጣይ ስላለው ሁኔታ ‹‹የቀረን ጥቂት ጊዜ ነው፡፡ መንግሥት ካመነብንና ጉባዔው ከመረጠን እንቀጥላለን፡፡ በቃችሁ ካለንም ለሚመጣው እናስረክባለን፤›› ብለው መግለጫውን አጠቃለዋል፡፡ 
በተያያዘ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ቡድኑን ውጤት ተከትሎ በመጪው ክረምት ሊደረገው የታሰበው የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ እንዲራዘምለት ለስፖርት ኮሚሽን ጥያቄ አቅርቧል ስለተባለው ጉዳይ አቶ ተካ፣ ‹‹ሁለት ወሩም ረዝሞብናል›› ሲሉ፣ አቶ ሳህሉ በበኩላቸው፣ ‹‹ጥያቄውን ያቀረበ የፌዴሬሽን አመራር የለም፤›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡          
   
            

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar