የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ
ታሪክ እንደሚያስረዳው የጎንደር ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ብዙ ዋጋ የከፈለ አሁንም እየከፈለ ያለ ነው፡፡ ለሀገር አንድነትና ሉአላዊነት ደንታ የሌለው የኢህአዴግ ስርአት የጎንደርን ድንግል መሬት ለሱዳን አስረክቧል፡፡ አባቶቻችን በደም የዋጁትን የሀገራችንን መሬት ለባዕዳን ያስረከቡ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለህግ እንዲቀርቡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በተለይም የጎንደር ነዋሪ የመጠየቅ ታሪካዊ ግዴታ አለበት፡፡ ኢህአዴግ ተጨማሪ መሬቶችን ለእየቆረሰ ላለመስጠቱ ምን ማረጋገጫ አለን? ሚሊዮኖች ሆነን ድምፃችንን ከፍ አድርገን የምንጠይቅበት ጊዜው አሁን ነው፡፡
Ø ኢትዮጵያ ዜጎች ሰርተው የሚኖሩባት፣ነግደው የሚያተርፉባት፣ልጅ ወልደው የሚያሳድጉባትና አስተምረው ለስራ ማብቃት የሚችሉባት ሀገር አልሆነችም፡፡ ስራአጥነት ተንሰራፍቶባታል፤ ዜጎች ዲግሪ ይዘው ኮብል ስቶን ፈላጭ ሆነዋል፣ በሀገራቸው ሰርተው መኖር ያልቻሉ ወጣቶች አስፈሪ የባህርላይና የበረሀ ጉዞዎችን በማድረግ ሀገር ጥለው ተሰደዋል፣በዋጋ ንረት አብዛኛው ዜጋ ያቃስታል፡፡ የነዚህ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምንጭ ኢህአዴግ የሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲ ነው፡፡ የስርአቱ ቁንጮዎች የተዘፈቁበት ሙስና ለችግሮቹ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡ በየጊዜው ከሀገራችን በህገወጥ መንገድ በኢህአዴግ ባለስልጣናት የሚወጣው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብም ከደሃው ጉሮሮ የተነጠቀ እንደመሆኑ ለህዝባችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል፡፡ ከስርአቱ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ጥቂት ግለሰቦች ተንደላቀው ሲኖሩ የተቀረው ህዝብ ግን በመኖርና ባለመኖር መካከል ይንገላታል፡፡ ታዲያ እስከመቼ በዋጋ ንረት ተቆራምደን፣በስራአጥነት ተንገላተን፣በስደት ክብራችንንና ህይወታችንን አጥተን፣ የበዪ ተመልካች ሆነን እንቀጥላለን? በሀገራችን ኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚ የመሆን መብታችንን ለማስከበር ጊዜው አሁን መሆን አለበት፡፡
በ ፀረ ሽብር ህጉ ሰበብ ከፌደራል መንግስት ተልከን መጥተናል የሚሉ የደህንነት ሀይሎች ጎንደር ላይ የፈለጉትን ሰው ማሰርና እንደዕቃ በአደራ ማስቀመጥን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡ በርካታ ዜጎች በቤተሰቦቻቸውና በወዳጆቻቸው ሳይጎበኙ በተለያዩ እስር ቤቶችና ስውር ማሰቃያ ስፍራዎች አበሳቸውን እያዩ ይገኛሉ፡፡ በአፋኙ የኢህአዴግ መንግስት የታሰሩ ወገኖቻችንን እንዲፈቱ አስቀድሞ ጥያቄ ለማቅረብ ከጎንደር ህዝብ የሚቀድም ማን ይኖራል?የፀረሽብር ህጉ እንዲሻርና በዚህ ኢህገ መንግስታዊ ህግ የታሰሩ ዜጎች በነፃ እንዲለቀቁ ለመጠየቅ የጎንደር ህዝብ በአደባባይ ድምፁን ያሰማል፡፡
Ø ኢህአዴግ ለዘመናት አንድ ሆኖ የኖረውን የጎንደር ህዝብ በዘር ለመካፋፈል ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡ የስርአቱ ማለሟሎች በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ለ22 እንዳደረጉት ሁሉ በጎንደርም አንዱን ቅማንት ሌላውን አማራ በማለት በነገድ ለመለያየት የሚያደሩት የክፋት ድር መበጣጠስ ያለበት አሁን ነው፡፡ አንድነታችንን ለማጥፋት የሸረቡትን ሴራ በአደባባይ ለማጋለጥ ጊዜው አሁን ነው፡፡
አንድነት ፓርቲ በነዚህና ሌሎች ህዝባዊ ጥያቄዎች ዙሪያ የጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ በገዢው ፓርቲ ላይ የማያቋርጥ ጫና ለመፍጠር ሀገር አቀፍ ተግባራዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በመሆኑ የዚህ ንቅናቄ አካል በመሆን ድምፃችንን በጋራ እንድናሰማ እንጠይቃለን፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar