ፓርላማው ጥርስ አወጣ ባይባልም እያሳከከው ይመስላል
ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ፓርላማው (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) ለየት ያለ ሁኔታ እየታየበት ነው፡፡ ለየት ያለ አዎንታዊ ሁኔታ፡፡
የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ባለሥልጣናት እንደተለመደው ለፓርላማው ሪፖርት ሲያቀርቡ በዝምና ጭጭ መንፈስ፣ በጭብጨባና በድጋፍ አጅቦ ከመቀበልና ከመሸኘት ይልቅ፣ በቀረበው ሪፖርት ላይ ጥያቄና ተቃውሞ ሲያቀርብ እየተደመጠ ነው፡፡ ችግሮች በግልጽ እንዲታዩና ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው ጠንክሮ ሲጠይቅም እየታየ ነው፡፡
ይህንን አዲስ ክስተት በመመልከት ተቻኩለን ፓርላማው ጥርስ አወጣ ወይም ጥርስ አበቀለ ባንልም፣ ጥርስ ለማውጣት እያሳከከውና እያነጫነጨው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የሰሞኑ ጥንካሬ ገጠመኝ ሳይሆን መርህ ሆኖ በዚህ ከቀጠለ ፓርላማው ጥርስ በማውጣት ነክሶ ማኘክና መዋጥ የሚችልበት ወቅት ሩቅ አይሆንም እንላለን፡፡
ይህን ስንል ግን ለፓርላማው ልዩ አንድናቆታችንን እየገለጽን አይደለም፡፡ ጥርስ ማውጣት፣ መንከስና ማኘክ የነበረበት በይፋ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነበር፡፡ ላለፉት ዓመታት ጥርስ ማብቀል፣ መንከስና ማኘክ ባለመቻሉ ምክንያት ጎደሎነቱን ከመውቀስና ከማማረር ይልቅ፣ አሁን በሚታየው ሁኔታ ፍንጭ በማሳየቱ ‹‹ወፌ ቆመች›› እያልን እናበረታታው፡፡
ፓርላማው ጥርስ እንዲያበቅል ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነበረበት፡፡ አለበትም፡፡ የበላይ አካል ነው፡፡ ሕገ አውጪ አካል ነው፡፡ ነፃ አካል ነው፡፡ ኃያል አካል ነው፡፡ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ለፓርላማው ታዛዥና የፓርላማውን ሕግና ውሳኔ ተግባር ላይ የሚያውል እንጂ፣ ከፓርላማው በላይ አስፈሪና አዛዥ አይደለም፡፡ ግን! ነገር ግን! በተግባር ሲታይ የበላይ አካል ሆኖ የተገኘውና ጎልቶ የተንፀባረቀው አስፈጻሚው ከሕግ አውጪው በላይ እንደሆነ ነው፡፡
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ባለሥልጣናት ማለትም ሚኒስትሮች በየጊዜው ለፓርላማው ሪፖርት ያቀርቡ ነበር፡፡ አዳምጦና አጨብጭቦ ከመሄድ አልፎ ይህን ለምን አልሠራህም? ይህንን አዋጅ የት አደረስከው? ብሎ የሚጠይቅ ፓርላማ አልነበረም፡፡
ለምሳሌ ያህል እንጥቀስ ከተባለ ፓርላማው ኢትዮጵያውያን ዜጎች የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ማቋቋም ይችላሉ ብሎ አዋጅ አውጥቶ ነበር፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ሪፖርት ሲያቀርብ ግን አዋጁን የት አደረስከው? እስካሁን ለምን የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ አልተቋቋመም? ብሎ ጠይቆ አያውቅም፡፡ በአጋጣሚ ቢጠይቅም ‹‹አይቋቋምም›› ብሎ አስፈጻሚው ሲመልስ ሕግ አውጪው ‹‹ሽምቅቅ›› ብሎ ሲርበተበት ነበር የሚታየው፡፡
አሁን ትንሽ ደፈርና ቀና ብሎ በበጀት አጠቃቀም፣ በኦዲት ሪፖርት፣ በተለያዩ ተቋማት የሥራ አፈጻጸም ላይ በሪፖርት አቅራቢዎች ላይ ፈርጠም ሲል እየተስዋለ ነው፡፡ ኃላፊነቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑን መገንዘብ የሚችል ኃይል መሆኑን ፍንጭ እያሳየ ይመስላል፡፡
ጥርስ አብቅሏል ባንልም ጥርስ ሊወጣ እያሳከከው ነው፡፡
ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ኃላፊዎችና ባለሥልጣናት ከሕግ በታች ናቸው፡፡ የበላዩ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ የበላይ ሕግ ነው፡፡ የበላይ ፓርላማ ነው፡፡ የበላይ የሕዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ ግን የተወሰኑ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና መሥሪያ ቤቶች የበላይ እየሆኑ የሕዝብ ወኪሎችን እያስፈራሩና እያሳነሱ ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል፡፡
ሕግ አውጪው (ፓርላማ) ጠንክሮ ሥራውን ሲሠራ፣ ሕግ አስፈጻሚው (መንግሥት) የድርሻውን ከተጫወተ፣ ሕግ ተርጓሚው (የፍትሕ አካል) ኃለፊነቱን ከተወጣና ሁሉም በሕጉ መሠረት ነፃ ሆነው ሥራቸውን ከሠሩ በእውነትም ሥርዓት ተገነባ፣ ተቋማት ተፈጠሩ ለማለት እንችላለን፡፡ ማለት ብቻ ሳይሆን ያኔ መኩራትም ይገባናል፡፡ ያኔ ነው ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት፣ ፍትሕ፣ ልማት፣ ሕልውናና ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ እውን የሚሆኑት፡፡
ፓርላማው ያሳየውን ጭላንጭል አጠናክሮ ተግባር ላይ ያውል፡፡ ከማሳከክ ወደ ጥርስ ማብቀል ይሸጋገር፡፡ አስፈጻሚው አካል ደግሞ ለዚህ ይዘጋጅ፡፡ ‹‹ተደነቀ፣ ተሞገሰ፣ ተበረታታ›› የሚሉ አደናጋሪ ቃላትን ከፓርላማው ሳይጠብቅ የት አደረስከው? ለምን አልሠራህም? ለምን አባከንክ? ለምን ሕግ ጣስክ? ተብሎ እንደሚጠየቅ ይመን፡፡ በሕዝብ ተወካዮች የተሾምኩ የሕዝብ አገልጋይ እንጂ ከሕዝብ ተወካዮች በላይ አይደለሁም ብሎም ይመን፡፡
በአገራችን ያለው ትልቁ ችግርና ድክመት ሥርዓትና ተቋማትን አለመገንባታችን ነው፡፡ የግለሰብ የበላይነት ከሥርዓትና ከተቋማት በላይ እየሆነ ነው፡፡ ሥርዓትና ተቋማት እስከገነባን ድረስ ግለሰቦች ከሥርዓቱና ከተቋማቱ ጋር ተስማምተው ይሠራሉ፡፡ ሥርዓትና ተቋማትን ካልገነባን ግን ተቋማትና ሥርዓት የእኛ መሣሪያና አገልጋይ ይሁኑ የሚሉ ባለሥልጣናትና ቡድኖች መጫወቻ ያደርጉዋቸዋል፡፡
ስለሆነም ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ በኋላና የፓርላማው የበላይነትና የሕግ አካላት ሕልውና ከተረጋገጠ ጀምሮ፣ ፓርላማው ጥርስ ሳያበቅል በመቆየቱ ጉድለቱን አምኖ ሕዝብን ይቅርታ እየጠየቀ፣ ካሁን በኋላ ግን ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቴን እወጣለሁ ይበል፡፡ እከታተላለሁ፣ እቆጣጠራለሁ፣ የሕግ አውጪነት ሚናዬን በተግባር አረጋግጣለሁ ይበል፡፡
ያኔ ነው ሕዝብ ፓርላማውን የሚያምነውና በፓርላማ የሚኮራው፡፡
አሁንም ፓርላማው ገና ጥርስ አላበቀለም፡፡ ግን ጥርስ ሊወጣና ሊበቅል ሲል የሚታየው የማሳከክና የመነጫነጭ ስሜት እየታየበት ነው፡፡ ተስፋ ሰጪ ነው እንላለን፡፡ በተለይም ኢሕአዴግ ከ99 በመቶ በላይ በተቆጣጠረው ፓርላማ የኢሕአዴግ የፓርላማ ተመራጮች ባለሥልጣናትን መቆጣጠር ሲጀምሩ ያኔ ነው እውነተኛው የአገር ህዳሴ የሚገለጸው፡፡
ከማሳከክ ወደ ጥርስ ማብቀል ያሸጋግራችሁ፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar