ኢህአዴግ የዲያስፖራ ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴውን ቀጥሎአል
ኢሳት ዜና:-የኢሕአዴግ መንግስት ዲያስፖራውን የስርዓቱ ደጋፊ ለማድረግ የቀየሰውን ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ በቅርቡ ከተለያዩ አህጉራት ከሄዱ የዲያስፖራ አባላት ጋር እየመከረ ሲሆን፣ ዲያስፖራው በአገር ውስጥ ስለሚያገኛቸው ጥቅሞች ገለጻ እየተደረገለት ነው።
ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት በሚልንየም አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ነዋሪነታቸው በውጭ አገር የሆኑ የስርዓቱ ደጋፊዎች መገኘታቸው የታወቀ ሲሆን ጠቅላላ ወጪያቸውም የተሸፈነው የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንሸስትመንት እንዲስፋፋ ከሰጠው የእርዳታ ገንዘብ ላይ ነው።
ዳያስፖራው በአገር ውስጥ ልማትና ዴሞክራሲ ተሣታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል የሚወጣው ፖሊሲ አተገባበሩ ላይ ውጤታማነት እንዲረጋገጥ አሁን ያሉ ህጐች ደንቦችና መመሪያዎች ሊሻሻሉ ይችላሉ» ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቴዎድሮስ አድሃኖም «ለዚህም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ጋር በመቀናጀት ዳያስፖራው የሚገጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ይጥራል» ሲሉ ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ «በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን በሚኖሩባቸው አገሮች ያለውን ግብር የመክፈል ባህል በአገር ውስጥ ለማስፋፋት የላቀ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል» በማለት ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
እራሱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር በሚል የሚጠራው ድርጅት ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር አባቡ ምንዳ የማነ ባደረጉት ንግግር ” የ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ጋር በመቀናጀት ዳያስፖራው የሚገጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ በመሆኑ ማህበሩን ተቀላቀሉ ብለዋል።
ይህ ማህበር የተቋቋመው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ ለቀብር ከውጭ አገር ቤት በሄዱ የስርዓቱ ደጋፊዎች ሲሆን በሙያው አንትሮፖሎጂስት የሆነው የማህበሩ ሊቀመንበር እርሱም ሆነ እመራዋለሁ የሚለው ማህበር የአቶ መለስን ራዕይ ለማስፈፀም ተግቶ እንደሚሰራ ደጋግሞ አስታውቋል።
በዕለቱ ዶር አባቡ በማኅበሩ ስም ከዶክተር ቴዎድሮስ እጅ የምስጋና የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን፣ ለአባይ ግድብ ቦንድ ግዢ ከፍተኛ ተሣትፎ አድርገዋል ለተባሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር ከሆኑት ደመቀ መኮንን እጅ የተሣትፎ ምስክር ወረቀት መቀበላቸው ታውቋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢህአዴግ በተለያዪ አገራት በሚኖሩ ደጋፊዎቹ በኩል ያዘጋጃቸው ስብሰባዎችና የአባይ ቦንድ ሽያጭ ዝግጅቶች፣ በከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ መሰናከላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የአዲስ አበባው ስብሰባ በድንገት የተዘጋጀውም ይህንኑ ተከትሎ መሆኑ መንግስት በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተለያየ መልኩ በመቅረብ በተደራጀ መልኩ እየተሰነዘረበት የሚገኘውን ተቃውሞ ለማርገብ የሚችልበትን ስልት ለመቀየስ ነው የሚሉ አስተያየቶች በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይቀርባል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢህአዴግ በተለያዪ አገራት በሚኖሩ ደጋፊዎቹ በኩል ያዘጋጃቸው ስብሰባዎችና የአባይ ቦንድ ሽያጭ ዝግጅቶች፣ በከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ መሰናከላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የአዲስ አበባው ስብሰባ በድንገት የተዘጋጀውም ይህንኑ ተከትሎ መሆኑ መንግስት በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተለያየ መልኩ በመቅረብ በተደራጀ መልኩ እየተሰነዘረበት የሚገኘውን ተቃውሞ ለማርገብ የሚችልበትን ስልት ለመቀየስ ነው የሚሉ አስተያየቶች በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይቀርባል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከሰሜን አሜሪካ ብቻ ከ300 በላይ የስር ዓቱ ደጋፊዎች ድንገት ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ አዲስ አበባ ማቅናታቸው ኢሳት ባለፈው ሳምንት የዘገበ ሲሆን፣ ከአውስትራሊያ ፣ ከአውሮፓና ከሌሎች አሕጉራት የሚኖሩ የኢህአዴግ ደጋፊዎችም ለዚሁ ተልእኮ ወደ ኢትዮጵያ ማቅናታቸው ታውቋል ሲል የአውስትራሊያው ቅዱስ ሃብት በላቸው ዘግቧል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar