መሬታቸው የተወሰደባቸው ከ50-60 የሚጠጉ የመተማ አርሶአደሮች ጫካ መግባታቸውን ሲያስታውቁ ከ30 ያላነሱት ደግሞ ታስረዋል
ኢሳት ዜና:- በመተማ ዮሐንስ እና በኮኪት ቀበሌዎች የሚኖሩ አርሶአደሮች መሬታችን አድሎአዊ በሆነ መልኩ ለባለሀብቶች እየተሰጠብን ነው” በማለት ተቃውሞአቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ ጸረ ሽምቅ እና ልዩ ሀይል የሚባሉ የመንግስት ታጣቂዎች ከ30 ያላነሱትን የአካባቢውን ሰዎች ሲያስሩ፣ በታጣቂዎች ከሚፈለጉት መካከል ደግሞ ከ50- 60 የሚሆኑት አርሶደሮች ጫካ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
ባለፉት ሳምንታት አቤቱታቸውን አዲስ አበባ ተገኝተው ለም/ል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም በባህርዳር ለአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ ካቀረቡት የህዝቡ ተወካዮች መካከል የተወሰኑት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ፣ ሌሎች ደግሞ ጫካ መግባታቸውን የህዝቡ ተወካይ የሆኑት እና በአሁኑ ጊዜ ጫካ መግባታቸውን የገለጹት አንድ አርሶአደር ገልጸዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በዛሬው እለት 30 የሚሆኑ እስረኞችን ከመተማ አውጥተው ወደ ሌላ ቦታዎች ለመውሰድ ሲሞክሩ፣ የአካባቢው ህዝብ አናስወስድም በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል። ይህን ዘገባ እሳከጠናከርንበት ጊዜ ድረስ በህዝቡና በመንግስት ባለስልጣናት መካከል የተፈጠረው ውዝግብ በምን ሁኔታ እንደተቋጨ ለማወቅ አልተቻለም።
በአሁኑ ሰአት ሽፍትነትን መርጠናል፣ ከማንኛውም የመንግስት ሀይል የሚመጣውን ጥቃት ለመመከት ተዘጋጅተናል” በማለት አስተባባሪው ገልጸዋል ።
ከተያዙት መካከል ከህዝቡ ጋር አብራችሁ መንግስትን ወግታችሁዋል የተባሉ ጥጋቡ አቸነፍ የተባለ የመተማ ወረዳ የሚኒሻ ኮማንደር እና ውብሸት የተባለ የቀበሌ ሹምም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
መንግስት መሬት በብሎክ የመከፋፈል አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ የአካባቢው ባለስልጣናት ለም የሆኑ መሬቶችን ለባለሀብቶች እና ለእነሱ ቀረቤታ ላላቸው ሰዎች ሰጥተዋል በሚል ተቃውሞ መቀስቀሱ ይታወቃል ።
የአካባቢውን ባለስልጣናትን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar