mandag 20. mai 2013

የበጀት ብክነትና ዝርክርክነት የሚታይባቸው ተቋማት ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው


የበጀት ብክነትና ዝርክርክነት የሚታይባቸው ተቋማት ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው


ሦስት ተቋማት በፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲመረመሩ ተጠይቋል
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ከ2004 ዓ.ም. በጀት ውስጥ 6.5 ቢሊዮን ብር በሕገወጥ መንገድ ወጪ መደረጉን ይፋ ካደረገ በኋላ፣ ባለፈው ዓርብ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የአስፈጻሚውን አካል አመራሮችና ሚኒስትሮችን ጠርተው በማነጋገር ማስተካከያ እንዲደረግ አስጠንቅቀዋል፡፡ 
ዋናው ኦዲተር ባቀረበው ሪፖርት መሠረት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከተፈቀደው በጀት በላይ መጠቀም፣ ከመንግሥት የተዝረከረከ ንብረት አያያዝና ከሕገወጥ ግዥ ጋር በተያያዘ የመንግሥትና የሕዝብ ጥቅምን እየጎዱ እንደሆነ፣ ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው የገንዝብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል፡፡ 
በሪፖርቱ ውስጥ የታዩት የግዢ ሥርዓትን የመጣስና ግዢዎችን በግልጽ ጨረታ ያለማካሄድ፣ ሕግና ሥርዓትን ጠብቆ ያለመሥራትና የገንዘብ አጠቃቀምን በተመለከተ መዝረክረክ እንደሚታይ አፈ ጉባዔው አስረድተዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥታዊ ተቋማት የሀብት አጠቃቀም ክፍተቶችን ለማጥበብ የውስጥ ኦዲት ሥርዓታቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ 
ችግሮቹን የውስጥ ኦዲት ሥርዓትን በማጠናከርና የበላይ ሚኒስትሮችና አመራሮች በአግባቡ ክትትል ቁጥጥርና በማድረግ ሊፈቱዋቸው ይገባል ሲሉ አፈ ጉባዔው መክረዋል፡፡ 
ከዚህ በኋላ ዋና ኦዲተር ተመሳሳይ ሪፖርት ለፓርላማው ቢያቀርብ ቀጥታ ወደ ዕርምጃ እንደሚገባ፣ ችግር ያለባቸው ተቋማት የሚያቀርቡዋቸው የበጀት ጥያቄዎችን ማስተናገድ ላይ ችግር ሊኖር እንደሚችል በመግለጽ አስጠንቅቀዋል፡፡ 
በውይይቱ ወቅት የመንግሥት መሥርያ ቤቶችን ወክለው የተገኙ ባለሥልጣናት ለየተቋማቱ የሚመደበውን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል የሚገባው በመሆኑ፣ የሚታዩትን ክፍተቶች ለማጥበብ እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸው ታውቋል፡፡
የምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተሾመ እሸቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዚህ በኋላ ጠንከር ያለ ዕርምጃ መውሰድ ዘመኑ የሚጠይቀው አስተዳደር ነው ብለዋል፡፡ 
ቋሚ ኮሚቴው በዘንድሮ በጀት ዓመት በዚህ ሕገወጥ ግዥና የሥራ አፈጻጸም ከፍተኛ ችግር አለባቸው ያላቸውን መሥሪያ ቤቶች በመለየት ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲከታተላቸው፣ አፈ ጉባዔው ደብዳቤ ለኮሚሽኑ በመጻፍ እንዲያስተላልፉ መጠየቁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 
የተቋማቱን ማንነት መግለጽ ያልፈለጉት ምክትል ሰብሳቢው፣ “አፈ ጉባዔው ለኮሚሽኑ መጻፍ አለመጻፋቸውንም እንከታተላለን፤” በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 
 

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar