ደቡብ ሱዳን ግጭቱ ተባብሷል፣እልቂቱ ከፍቷል፣የተፈናቃዩ ቁጥር ጨምሯል፣ድርድሩ አልሰምር ብሏል፣ ጠቅላይ ሚኒስትራችንና ውጪ ጉዳይ ምኒስትራቸን ሥራ በዝቶባቸዋል፡፡
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ምክትላቸውን ከሥልጣን ማባረረረራቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ግጭት እንበለው ጦርነት አንድም ኢትዮጵያ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በመሆኗ፣ሁለትም ወሰን ተጋሪ ቅርብ ጎረቤት ሀገር በመሆኗ ሶስትም ተመሳሳይ ጎሳዎች እዚህም እዛም ያሉ በመሆኑ አራትም አዲሲቷ በነዳጅ የከበረች ሀገር ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ ቦታ በመሆኗ ወዘተ ምክንያቶች የተቀሰቀሰው ግጭት ኢትዮጵያን በጣሙን ያሳስባታል፡፡ ይህም በመሆኑ ነው ሁለቱ ምኒስትሮች ፋታ ማጣታቸው፡፡
ነገሩ ወደ ጎሳ ግጭት እንዳያመራ ያሰጋል፣ውጪ ጉዳይ ምኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም 2006 ከጅምሩ ሥራ አብዝቶባቸዋል፡፡ሰውዲ አረቢያ ከሀገሬ ውጡ በማለት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈጸመችባቸው ኢትዮጵያዉያንን ጉዳይ ከጅምሩ ተገቢ ትኩረት ባይሰጠውም የዓለም የመገናኛ ብዙኋን በማስተጋባታቸውና ተቀዋሚዎችም በሀገር ወስጥም በተለያዩ ሀገራም ሰላማዊ ሰለፍ በመውታት ጭምር ሰወዲን በኢሰብአዊ ድርጊ ቷ እኛን መነንግስት ደግሞ በቸልተኝነቱ በማውገዛቸው መንገሥት በእቅድ ሳይሆን በግብታዊነት የገባበት ወደ ሀገር የመመለስ ስራ ላይ ዋንኛ ባለድርሻ ሆነው የታዩት ዶ/ር ቴዎድሮስ ናቸው፡፡ስራው ደንገቴ ከመሆኑ በላይ የተመላሾቹ ቁጥር ከተገመተው አይደል ሊታሰብ ከሚችለው በላይ መሆኑ ደግሞ ሌላው ራስ ምታት ነበር፡፡
ይህ ሳይጠናቀቅና መልክ ሳይዝ በጎረቤት ደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የመንግሥት ያለህ፣ከዕልቂት አድኑን፣ከጦርነት እሳት አውጡን የሚል የዜጎች ጩኸት በመሰማቱ በእንቅር ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል፡፡
በዚህ ውጥረት ወስጥ የሚገኙት ዶ/ር ቴዎድሮስ የደቡብ ሱዳን ግጭት ተባብሶ እልቂት ከመንገሱ በፊት ለግጭቱ ምክንያት የሆኑትን ፕሬዝዳንቱንና ም/ል ፕሬዝዳንቱን ወደ ድርድር ለማምጣት ከአዲስ አበባ ጁባ ተመላልሰዋል፡፡ነገሩ ተባብሶ ወደ ጎሳ ግጭት እንዳያመራ ያላቸውን ስጋትም ገልጸዋል፡፡
በጎሳ ላይ በተመሰረተ የሥልጣን ክፍፍል ከያዙት ሥልጣን አንዱ አባራሪ ሌላው ተባራሪ ሲሆን ጉዳዩ የሁለቱ ሰዎች ብቻ ሆኖ ሊቆም፣ በፖለቲካ መንገድ ብቻ ሊስተናገድ አይቻለውምና ወደ ጎሳ ግጭት ማምራት አይደለም ሲጀመርም በዛው መልክ ነው የሚነሳው፡፡ ሹመታቸው በጎሳቸው እንደመሆኑ ጸባቸውም ጎሳዊ ነው የሚሆነው፡፡ ስለሆነም አስፈሪው የጎሳ ግጭት መቼም የትምና በማንም እንዳይነሳ ዋናው መፍትሄ ከመነሻው ፖለቲካው በጎሰኝነት ዜማ የሚዘፈንበት እንዳይሆን ማድረግና የሥልጣን ክፍፍሉ ጎሳን መሰረት አድርጎ ታማኝ ከሆነ ዘበኛም ቢሆን ምኒስትር አድርገን እንሾማለን እየተባለ የሚፈጸም ሳይሆን በእውቀትና በብቃት ብሎም በሕዝብ መራጭነት ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡
ውጪ ጉዳይ ምኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ ደቡብ ሱዳን ተገኝተው የተመለከቱት ከአቻዎቻቸው ፖለቲከኞች ጋር ሲነጋገሩ የተገነዘቡት አሳስቧቸው ወደ ጎሳ ግጭት እንዳይሸጋገር መስጋታቸውና ይህንኑ በአደባባይ በይፋ መግለጻቸው ተክክል ቢሆንም እውነቱ የተከሰተላቸው በሰው ቤት ያውም ግጭት ተቀስቅሶ ደም ከፈሰሰ በኋላ መሆኑ ነው አጠያያቂው፡፡
እኛ ቤት፣ ከኢትዮጵያዊነት ጎሰኝነት ቀድሞ መጀመሪያ በየጎሳችሁ ተበታትናችሁ ከዛ በኋላ ኢትዮጵያን በመፈቃቀድ እንመሰርተንለን የሚል ቅዠት ተፈጥሮ፣ እንትንነቴን(ጎሳውን) የማታረጋግት ኢትዮጵያ ትበታትን እየተባለ ተፎክሮ በአንድ ሰሞን የፖለቲካ ስካር ወገን በወገኑ ላይ ጦር እንዲመዝ መደረጉ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ አንደ እየምነቱ ለፈጣሪው የሚገዛ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የቀጠለ ጨዋነት የባህሪው መሆኑ እንጂ አንደ ፖለቲከኞቹ ፍላጎት ቢሆን ኢትዮጵያ በዛሬ መልኳ መታየት ባልቻለች ነበር፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ማንም በምንም መንገድ ሊያጠፋው አይችልም፡፡ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም በ1986 ዓም ኢትዮጵያ ከየት ወዴት በሚል ርእስ በጻፉት መጽሀፍ ገጽ 32 ላይ «የኢትዮጵያ ታሪክ ሊያስተምረን እንደሚችለው ኢትዮጵያዊነት አንደ ላስቲክ ነው ሲስቡት ይሳባል፣ሲለቁት ይሰበሰባል ፣ ማለት ይሳብና ይሳሳል እንጂ አይበጠስም» ይላሉ፡፡ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞቹ ካልተሳካው ተግባራቸው ይህን መረዳታቸው ባያጠራጥርም አልሆንልህ አለኝ አጉራህ ጠናኝ ብለው ወደ ትክክለኛው መስመር መመለስን ሽንፈት አልያም ውርድደት ሆኖባቸው እንደ አጀማመራቸው ባይሆንም ዛሬም ጎሰኛነትን ከማቀንቀን አልተመለሱም፡፡
ለሥልጣን መሰረቱ ለሹመት መስፈርቱ የጎሳ ድልድል ሆኖ ማስፈጸሚው ደግሞ በስም ለኢህአዴግ በተግባር ለህውኃት ብሎም ለወሳኞቹ ባለሥልጣኖች ታማኝ ሆኖ መገኘት ሀኖ ያሟላሉ ተብሎ ታምኖባቸው የተሾሙ ወደ ህሊናቸው ሲመለሱ፣ ወይ ታማኝነታቸውን ሲያጓድሉ፣ አልያም እንደታሰቡት ሆነው ሳይገኙ ሲቀሩ በሙስና ወይንም በመተካካት ሰበብ ለእስር ሲዳረጉ ወይንም ሲገለሉ፣አለያም ከሥልጣን ዝቅ ሲደረጉ ድርጅታቸውም ሆነ ጎሳቸው ድምጽ አለማሰማታቸው የእርምጃውን ትክክለኛነት የጎሳ ሥልጣን ክፍፍሉን ጤናማነት የሚያረጋግጥ ተደርጎ ታስቦ ከሆነ ስህተት ነው፡፡
ድርጅቶቹ (ፓርቲዎቹ) ምንም አለማለታቸው አፈጣጠራቸውም ሆነ እድገታቸው ለዚህ የሚያበቃ ነጻነት የሌለቸው በመሆኑ ሲሆን ( የሁሉም ፈጣሪ ህውኃት ስለመሆኑ ፈጣሪውም ተፈጣሪውም በኩራት የሚናገሩት ነው) የጎሳቸው ዝምታ ደግሞ መጀመሪያም ውክልናቸውን አለመቀበሉ ሁለተኛም የሾማቸው አነሳቸው በሚል አይመለከተኝም ስሜት እንደሚሆን ይገመታል፡፡
ፕ/ር መድሀኔ ታደሰ በ1996 ዓም ከአንድ በሀገር ውስጥ ይታተም ከነበረ መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ «ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አለባቸው ስትል በርግጠኝነት ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አለባቸው፤አሁን በክልል ይሄ ነው ችግሩ፡፡ ከዚህ በላይ ግን ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ማስተዳደር ያልቻሉ ክልሎች ክልላቸውን እንኳን ቢያስተዳድሩ በቂ አይደለም፡በማዕከላዊ መንግሥት ጭምር በውሳኔ ሰጭነት ጭምር መሳተፍ ነበረባቸው፡፡ይህ በሌላበት ሁኔታ የብሔር ጭቆናን መሰረት ያደረገ ሥርዓት መሥርተህ ልትተገብረው ካልቻልክ ጭቆናውን በማባባስ የበለጠ ግጭት እንዲፈጠር ነው የሚያደርገው» በማለት የታሰበው በሚነገርለት ደረጃ እንኳን ተፈጻሚ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአስተዳደር ክልልን በጎሳ የሹመት ድልድልን በጎሳ፣የፖለቲካውን ቅኝት በጎሳ፣ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በጎሳ፣ ወዘተ መቃኘቱ የመጀመሪያው ችግር ሆኖ ይህንኑ በሚነገርለትና በህግ በተጻፈው አግባብ ተግባራዊ አለማድረግ ሁለተኛው ችግር ነው፡፡ በየቦታው በፖለቲካ ፓርቲ መሪነትም ሆነ በክልል አስተዳዳሪነት የሚቀመጡ ሰዎች አመኔታ የሚያጡት ብዙ የሚባልለትን እኩልነት በተጨባጭ ተግባራዊ ለማድረግ በአለመቻላቸውና እንወክለዋለን ከሚሉት ህብረተሰብ ይልቅ ታማኝነታቸውም አገልጋይነታቸውም ላስቀመጣቸው ሀይል መሆኑ ነው፡፡
ነብሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ ሳይታሰብ በድንገት በሞት ሲለዩን አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ወደ ጎን ሊገፉ የማይቻልበት ቦታ ላይ በመገኘታቸው ምክንያት ሙሉው ሥልጣን ባይኖራቸውም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ሲይዙ በህውኃት ሰፈር አሰረክባችሁ መጣችሁ በሚል ጥያቄ መነሳቱን ውስጥ አዋቂዎች በተለያዩ የመረጃ ማስተላለፊያ መንገዶች ገልጸውታል፡፡ በአቶ መለስ የሁለት አሥርት አመታት የሥልጣን ዘመን ያልነበረ የሶስት ምክትል ጠቅላይ ምኒስትሮች ሥልጣን የተፈጠረውም ይህንኑ የህውኃትን ጥያቄ ተከትሎ እንደሆነ ነው የተነገረ የተጻፈው፡፡
ሌሎቹ ድርጅቶች ነጻነታቸውን አረጋገጥው በየራሳቸው እግር መቆም ከቻሉ ተመሳሳይ ጥያቄ ሊያነሱ እንደሚችሉ አያጠያይቅም፡፡ ጥያቄውም ከፖለቲካዊነቱ ጎሰኛነቱ ስለሚያመዝን ለምላሽ ያስቸግራል፣ ውጪ ጉዳይ ምኒስትራችን በደቡብ ሱዳን እንዳይፈጠር ወደ ሰጉት የጎሳ ግጭትም ሊያመራ ይችላል፡፡ ዮሀንስ ገብረማሪያም የተባሉ ጸሀፊ በ1987 ዓም በጦቢያ መጽሔት ጎሰኞችና ጎሰኝነት ያሳፍራሉ ያስፈራሉ በማለት ባሰፈሩት ጽሁፍ «ጎሰኝነት ብዙውን ግዜ ሌሎች ጎሳዎች አደረሱብን የሚሉትን ይም ደርሶብናል ብለው የገመቱትን ጥቃት ለመመከት ወይም ደግሞ ሆን ብሎ ሌሎችን ለማጥቃት የሚውል የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው፡» ብለዋል፡፡ ጎሰኝነትን በሚያቀነቅኑ ወገኖቸ የሚካሄድ ቅስቀሳን አደገኛነትም ሲገልጹ «ይህ ቅስቀሳ አውቆ አበዶችን ብቻ ሳይሆን መሰሪነቱን ያልተረዱ ብዙ የዋህ ተከታዮችን ሊያስገኝና ሊያሳስትም ይችላል» ይላሉ፡፡
ዛሬ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ገመድ ተሸብበው ፣በማሌ አደረጃጀት ተቆላልፈው፣ በአንድ ለአምስት ተጠርነፈው ህውሀት በቀደደላቸው ቦይ ቢፈሱም አንድ ቀን ግድቡን ጥሶ አልያም መስመሩን ለውጦ ሊፈስ እንደሚችል ያን ግዜ ደግሞ ለቁጥጥርም ለድርድርም እንደሚያዳግትና ከፍተኛ ጥፋት ሊያደርስ እንደሚችል ሌላው ቢቀር በደቡብ ሱዳን ከሚታየው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለሆነም መሪዎቻችን የደቡብ ሱዳንን ችግር ለመፍታት እየሸመገሉ ከሂደቱ ለራሳቸውም ቢማሩ መልካም ነው፡፡ አስተዋይ ከጎረቤቱ ይማራልና፡፡
የተዳፈነው እሳት ተግለጦ ከተቀጣጠለ፣በድርጅታዊ ቅርጫት ያስገቡት አፈትልኮ ከወጣ ማጣፊያው እንደሚያጥር፣ ነገሩ እንደሚከርና መዘዙ ብዙ ነገር እንደሚመዝ የደቡብ ሱዳኑ ጉዳይ ቅርብና ግልጽ ማሳያ ነውና አንማርበት፡፡
ስለሆነም ዛሬ የጎሳ ፖለቲካ ደቡብ ሱዳን ላይ ስጋት መሆኑ የታያቸው ውጪ ጉዳይ ምኒስትራችን አንድ ቀን እኛም ቤት አደጋ ሊሆን እንደሚችል በማጤን ፖለቲካችንን ከጎሳ ሰገነት ላይ ለማውረድ ቢሰሩ ለርሳቸው ክብር ለሀገርና ለሕዝብም ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ማስገኘት ቻሉ ማለት ነበር፡፡
ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርደር፣
ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርደር፣
ጠቅላይ ምኒስትራችን የወቅቱ የአፍረካ ህብረት ሊቀመንበር፣የቅርብ ጎረቤት ሀገር መሪ ወዘተ አንደመሆናቸው በደቡበ ሱዳን ግጭት አንደተቀሰቀሰ ፈጥነው ወደ ከቦታው በመድረስ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት መፍትሄው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር መጀመር እንደሆነ መናገራቸውን ከዜና ማሰራጫዎች ሰምተናል፡፡ ሀሳቡ የቀረበው ጥይት ከተተኮሰ ደም ከፈሰሰና አቅም ከተፈተሸ በኋላ በመሆኑ ያለቅድመ ሁኔታ የሚለው የተወሰኑ የሀገሪቱን ቦታዎች በመቆጣጠር አቅሙን በፈተሸው አማጺ በኩል ተቀባይነት አላገኘም፡፡ እንደውም ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በመንግስት በኩል በጎ ምላሽ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ከሁለቱም ወገን ተደራዳሪዎችን አዲስ አበባ ማምጣት ቢቻልም ይህ ጥሁፍ ወደ ዝግጅት ክፍሉ እስከተላከበት ቀን ድረስ በግንባር ማገናኘት አልተቻለም፡፡
ጠቅላይ ማኒስትራችን ከዚህ ሂደት ሁለት ነገሮችን ይገነዘባሉ ብለን አንገምት፡፡ አንድ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ድርድር ለደቡብ ሱዳን ብቻ ሳይሆን ለእኛም ሀገር ችግር መፍትሄ መሆኑን ቢያምኑበትና ለተግባራዊነቱ አቅማቸውም ነጻነታቸውም የሚፈቅደውን ቢያደርጉ፡፡ ሁለት በሥልጣን ላይ ያለ ሀይል ከተቀዋሚዎቹ ጋር ለመነጋገርም ሆነ ለመደራደር ሸብረክ የሚለው ብረት አንስተው ዱር ቤቴ ሲሉ ብረት ያነሱትም አቅማቸውን ከፈተሹና ነጻ መሬት መያዝ ከጀመሩ በኃላ መሆን እንደሌለበት አቶ ኃይለማሪያም እየሸመገሉ ቢማሩ በአጭሩ የሥልጣን ዘመናቸው የዘለዓለም ክብር የሚያቀዳጃቸው ተግባር ፈጸሙ ማለት ነበር፡፡
ክቡር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስመ ሥልጣኑን በመሀላ ከተቀበሉ በኋላ ሀላፊነታቸው የቀድሞውን ጠቅላይ ምኒስትር የመለስን ሌጋሲ ማስቀጠል መሆኑን በመግለጻቸው ሰላማዊ ትግል ከመረጡት ጋር ለመነጋገርም ሆነ ኢህአዴግን ማነጋገር በሚገባው ቋንቋ ነው ከሚሉት ጋር ለመደራደር የሚቀርቡ ጥያቄዎችም ሆኑ የተሞከሩ ጅምሮች የማይታለፉ ቅድመ ሁኔታዎች እየቀረቡ ተሰናክለዋል፡፡ ትናንት ዛሬ እንዳልሆነ ሁሉ ነገም ዛሬ አይሆንምና ዛሬ የገፉት የንግግርም ሆነ የድርድር ጥያቄ ነገ ፈልገው ለምነው የማያገኙት ሊሆን ይችላልና ወዳጅ ሳይርቅ ጉልበት ሳይከዳ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ንግግርም ደርድርም መጀመር ለሁሉም ይጠቅማል፡፡
በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ የታህሣሥ 30/2006 ላይ የወጣ
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar