lørdag 11. januar 2014

አዲስ ዓመት ለጋራ ራዕይ – በአበራ ሽፈራው /ጀርመን/


በፈረንጆቹ ወይም እንደ ጎርጎርያን አቆጣጠር 2013 ዓ.ም  በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው አለም ታላላቅ አሳዛኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ግጥመውን አልፏል፡: አንዳንዴም ይህ ዓመት ባልነበረ የሚያስብል ነበር :: እንኳን አለፈ ::
ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ብዙዎች ለእስር የተዳረጉበት፣ ፍርደገምድል ፍርዶች በፍርድ ቤቶች የታዩበት፣ የፖለቲካ እስረኞች በከፍተኛ ሁኔታ የተበራከቱበት፣ እስር ቤቶች በፖለቲካ አቋማቸውና አስተሳሰባቸው ብቻ በህወሓት ሰዎች አይን ውስጥ በገቡ የተሞሉበት ፣ የነጻው ፕሬስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በህወሓቶች ጥቃት የደረሰበት ፣ የአማራ ተወላጆች በዘረኞችና ግልጽ በወጣ የዘር ጥቃት በሚፈጽሙ በህወሃቶች ባለሟሎች እቅድ ማፈናቀል የተደረገበት በዚህም ምክንያት ብዙዎች ለመከራና ለችግር የተዳረጉበት፣ አጥፊው የህወሓት ማኔፌስቶም አሁንም ትግበራውን ይቀጥላል ማኔፌስቶው ሳይሆን ምስጊን የቤንሻንጉልና ጉምዝ ሰዎች በትግበራ ዙሪያ እንደደቡቡ በተጠና መልኩ ማፈናቀሉን ባለማድረጋቸውና ህወሓቶችን በአደባባይ ያጋለጠ ድርጊት በመሆኑ ለቅጣት ተዳረጉ፣ አዛዡ አሳሪ ታዛዡ ታሳሪ ሆነናድራማው ተጠናቀቀ በዚሁ ክፉ ዓመት : : በተለይም የሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሃይማኖት ነጻነት ትግልን በሃይል ለመጨፍለቅ ታስቦ ብዙዎች በአደባባይ የተገደሉበት፣ የታሰሩበትና እጅግ አስከፊ ግፍ የተፈጸመበት ዓመት ነበር በአገራችን ኢትዮጵያ::
ይኸው 2013 የህወሓት ዘረኛ ቡድን የአገሪቷን ወታደራዊ ኃይል ለመቀራመት በድርጊቱ ጠንሳሽና መሃንዲስ በነበረው መለስ ዜናዊ እቅድና ራዕይ መሰረት ሁሉንም ወታደራዊ ሃይል በህወሓቶች ለማስያዝና የአፈናውን ሥርዓት ለማጠናከር ሲባል በየትኛውም የአገሪቷ ዘመናት ባልታየ መልኩ ከፍተኛ የጀነራልነት ማዕረጎችና ሌሎች ወታደራዊ ሥልጣኖችን 99% በሚባል መልኩ የህወሓትን የበላይነት ለማረጋገጥና ስርዓት የለቀቀውን አገርን የመምራት አቅም ማጣት ለማስጠበቅ ሲባል ምንም ወታደራዊ አቅምና ትምህርት ለሌላቸው ሰዎች ብዛት ያለው የጀነራልነት ማዕረጎችን በመስጠት በአለምና በአገሪቷ  ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የሹመት ድግስ የተደገሰበት ዓመት በመሆን ተመዝግቧል ::
በዚሁ በ2013 የሰላማዊ ትግል አራማጅ ፓርቲዎች በአገር ውስጥ በተለይም የአንድነት ፓርቲ፣ የሰማያዊ ፓርቲና የመድረክ አመራሮችና አባሎቻቸው ለከፍተኛ ጥቃት የተጋለጡበት፣ በየምክንያቱ አባሎቻቸው ለእስር፣ ለድብደባና ለእስራት የተዳረጉበት ጊዜ በመሆን የሥርዓቱ አስቸጋሪነትን የተመለከትንበት ዓመት በመሆን አልፏል :: የተቃዋሚው ሃይል ከገዢው የማፍያ ቡድንም ጋር  ግልጽ የሆነ ትንቅንቅ ውስጥ የገባበትና የህወሓት ገዢ ቡድንም በከፍተኛ ትዝብት ላይ የወደቀበት ጊዜ በመሆን የተሰናበተን ዓመት ሲሆን በተቃዋሚው ላይ የደረሰው መከራ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሆነበት  ዓመት ለመሆን በቅቷል ::
አገራችንና ህዝቦቿ በእነዚህ ሙሰኞችና በዝባዦች እጅ ከወደቀችበት ጊዜ ጀምሮ ፍጹም ባልታየ መልኩ ጥቂቶች እየበሉና እየጠጡ የሚኖሩባት ሌሎች ወይም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለፍጹም የኑሮ ውድነት የተጋለጠበት ዓመት ከመሆኑም በላይ በኑሮው ውድነት ምክንያትም ህዝቡ ለከፍተኛ የኑሮ ምስቅልቅሎሽ ተዳርጎና ለከፍተኛ ስደትም በመዳረግ በልዩ ልዩ ቦታዎች የሚደርስበት የስደት መከራና ሞት ቀላል አልነበረምና አብዛኛው ህዝቡ ችግሩን ተጋፍጦ መፍትሄ የሚያመጣለት አጥቶ አምላክን በመማጸን ያሳለፈበት አመት በመሆን አልፏል :: ይሁንና ህወሓቶችና ባለሟሎቻቸው ግን በየምክንያቱ ጮማ እየቆረጡና ውስኪ እየተራጩ ዓመቱን ሲያሳልፉ መክረማቸውንና በተለያዩ አገራት ያሸሿቸው የገንዘብም መጠን ቀላል እንዳልሆነና ከሟቹ መሪያቸው ጀምሮ እስከ ትልልቅ ሹማምንቶቻቸው ድረስ የአገሪቷን ገንዘብ ለመበዝበዛቸው የውጭ ሚዲያዎችና እራሱ ኢቲቪ ሳይቀር ተገዶ “ሙሰኞች ነን” ለማለት የሞከሩበት አመት ሆኖ ተመዝግቧል :: ይሁንና ከዚሁ ከሙስና ጋር ተያይዞ ሙሰኛ ጋኖችን ሳይሆን ሙሰኛ ገንቦዎችን በመስበር ሲቀልዱ የታዩበት ዓመት ነበር :: ከዚህም የተረዳነው የጠገቡ ሙሰኞች ያልጠገቡ ሙሰኞችን ሲያጠቁ ተመለከትን ::
በዚሁ ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት ህወሓት በታሪክ አጋጣሚ ከሱዳን ጋር ባለው የጥፋት ቁርኝት አገርን ለባእዳን አሳልፎ በመስጠት የሚታወቀው ሥርዓት ከኢትዮጵያ ድንበር ሰፊውን ግዛትና ለም የሆነውን የአገሪቷን መሬት ለሱዳን ለመስጠት ውሎችን ለመፈራረምና ለዘመናት ደም እየተከፈለበት የኖረን የአገሪቷን መሬት አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀበትና ህወሓት ምን አልባትም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያስብ ቡድን እንኳን ሆኖ ቢገኝ በአገሪቷ ታሪክ በክህደት የሚጠየቅበትን ሁኔታ ያስመዘገበበት አመት ሆኖ ከመመዝገቡም በላይ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከአሰብና ከሌሎች በህወሓት ምክንያት ደም ካፋሰሱ የኢትዮጵያ ድንበሮች በተጨማሪ አሁን ደግሞ በዚህ ዘመን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አገርን ለመሸጥ ሲደራደሩ የከረሙበት ዓመት በመሆን ተመዝግቧል ::
የብዙዎች የኢትዮጵያ ሱማሌዎችና የአፋር ህዝቦች ደምም በህወሓት ወታደሮች የፈሰሰበትና ህወሓቶች በሌሎች ዓለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ግፍ የፈጸሙበትን ማስረጃ የቀረበበት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውንና ማስፈጸማቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎች የተገኙበትና ያንንም ለማጠናከር ትልቅ ግልጽ ዘመቻ የተከፈተበት ዓመት በመሆን በአውሮፓዊቷ አገር በሲውዲን አገር እንቅስቃሴ የተጀመረበት ዓመት በመሆንና ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን ለማጠናከር እንቅስቃሴ የተጀመረበት ዓመት በመሆንም ይታወሳል 2013 ::
“አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል ” እንዲሉ ዘረኛውና አንባገነኑ የህወሓት መሪ ለ21 ዓመታት ለብቻው ይዞት የነበረው የጭቆና ቀንበር ለዘለዓለም ወደዚች ምድር ላይመለስ በሞት በመሰናበቱ ምክንያት አገሪቷን ለከፍተኛ ችግርና አዳጋች ሁኔታ አጋልጧት እንደሄደና ህወሓትንም እርቃኑን አስቀርቶት ባዶ ቡድን መስርቶ የነበረ ለመሆኑ ማስረጃ መሆኑ እስኪታይ ድረስ ተተኪን ለመፍጠር እንኳን እንዳይቻል እያስፈራራ የፈጠረውና የገነባው ሥርዓት ለመሆኑ በግልጽ እስከሚታይ ድረስ በህወሃቶች መካከል ብቻ ሳይሆን በተለጣፊዎቹ የህወሃት ኢህአዴግ ፓርቲዎች ጭምር የዕርስ በርስ ትርምስ የተፈጠረበትና አገሪቷን የሚመሩ ግማሽ ደርዘን ሊጠጋ ትንሽ ቁጥር የቀረው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን በመያዝ የተመዘገበችም አገር በመሆንና ኢትዮጵያውያንን በማስገረም ያለፈ ዓመት ሆኖ አልፏል ይኸው 2013 ጉደኛ ዓመት ::
ይኸው 2013 በአባይ ግድብ ሰበብ ከመላው ኢትዮጵያና ከመላው ዓለም ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኪስ የህወሓት ቀማኞች ገንዘብ የሰበሰቡበት፣ በግዳጅ የነጠቁበትና ገንዘባቸውን ለቀማኛ ቡድን ለመስጠት ያልፈለጉ በውጭው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የአባይን ግድብ እንዲገደብ ቢደግፉም በብዝበዛ፣ በሙስናና በመስረቅና የሃገርን ሃብት በውጭው ዓለም በሚገኙ ባንኮች በማስቀመጥ የሚታወቁትን የህወሓት የማፍያ ቡድንን ከአባይ በፊት ሰብዓዊ መብት እንዲያከብሩ በመጠየቅ፣ መለስና ሌሎች የህወሓት ሰዎች በውጭ ያከማቿቸው ገንዘቦች አንድ አባይን አይደለም ብዙ አባይን ይገነባሉና አውጡና በአገራችሁ አውሉት እያሉና ሌሎች ተመሳሳይነት ያላቸውን ሃሳቦች በማንሳትና በመቃወም በመላው ዓለም ህወሓት የቀለለበት ዓመት ነበር 2013 በእርግጥም ሕወሓት ቀድሞውንም ቢሆን በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት የቀለለ ለመሆኑ እራሱ ህወሓትም ያውቀዋል ::
በዚሁ በ2013 በአገራችን በተለይም በጋምቤላ ክልል ሰፊ የመሬት መቀራመት የተፈጸመበትና ከፍተኛ ተቃውሞም በዚሁ ዙሪያ የተደረገበት ዓመት ከመሆኑም በላይ የጋምቤላ ነዋሪ ወገኖቻችንም በተወለዱበት፣ በአደጉበትና ተፈጥሮና ትውልድ ያስረከባቸውን መሬት በህወሓት ቀማኞች በአደባባይ በሃይል የተነጠቁበት ዓመት ነበር :: በሌሎች ክልሎች የገጠር ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በከተማ ቦታዎችም ዙሪያ ግልጽ ቅሚያ የተፈጸመበትና ህወሓትን ተው የሚለው ጠፍቶ ያሻውን ያደረገበት ዓመት ነበር ::
የህወሓት አንዱ የመበዝበዣ ተቋም የሆነው የመከላከያ ሚንስቴር መስሪያ ቤትና ተያያዥ መምሪያዎችና የወታደራዊ መዋቅሮች በአገሪቷ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአንድ ዘር ስር መውደቁ የታወቀ ቢሆንም የአገሪቷ ሃብት በዚሁ ተቋም በነዚሁ በህወሓት ጀነራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች እንደሚበዘበዝ ግልጽ እየሆነ ባለበትና ወቅትና ይህንንም ችግር ለማስቆም የተለያዩ አካላት ጥያቄ ማንሳት በጀመሩበት ወቅት ማንም ምንም አያመጣም ያሉ እስኪመስል ድረስ መከላከያ ኦዲት አይደረግም የሚል ሃሳብ መነሳቱና ጉዳዩ የህግ ከለላ እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸው የታየበትና ጉዳዩ በግልጽ እንደሚያሳየው ብዝበዛው በህግ እንዲደገፍ አዋጅ ያስነገሩበት ዓመትም ነበር በእርግጥም አይን ያወጣ ዝርፊያ ለመቀጠል ከፍተኛ መሰረት የተጣለበት ነበር ይህ ክፉ ዓመት:: አይ 2013 ጉደኛ ዓመት ::
የህዝቡን የፍትህና የነጻነትን ጥማት ይልቁንም ለመቀልበስና የህወሓትን ብዝበዛና ጭቆናን ለመቀጠል በታሰበ መልኩ “1 ለ 5″ የሚልን የአፈና መዋቅር ለመተግበር ከፍተኛ ርብርብ የተደረገበትም ዓመትም ነበር::
በሌላ በኩል  በዚሁ አስከፊ ሥርዓት ምክንያት በዓረቡ ዓለም ተበትነው የሚኖሩና በተለይም በሳውዲ አረቢያ በልዩ ልዩ መንገድ ወጥተው ተቀጥረው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ በደረሰው ችግርና ሰቆቃ ምክንያት ብዙው ኢትዮጵያዊ በዓለም ህዝብ ፊት በዕንባ የተራጨበትና አምላክንም የተማጸነበት ዓመት ሆኖ ነበር :: በዚህ ምክንያት ብዙ ኢትዮጵያውያን ውስጣቸው ያዘነበት ዓመት ነበር::

ይህም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ህወሓትን ለመጋፈጥና በግልጽ መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጠበት፣ የሠላማዊ ትግል አራማጆችም ትግሉን በተለያዩ አቅጣጫዎች ያደረጉበትና የህወሓትን ማንነት በማሳወቅ ዕርቃኑን እንዲቀር ያደረጉበት ፣ የትጥቅ ትግል አራማጆችም ትግሉን በተለያየ አቅጣጫ በማድረግ ህወሓት ድንጋጤ ውስጥ እንዲገባና የሚይዘውና የሚጨብጠው እንዲያጣ በማድረግ ያደረጉት ትግልም ቀላል አልነበረም:: በዚህ ዙሪያ አርበኞች ግንባር፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦጋዴን ነጻነት ግንባርና ሌሎችም ያደረጉት የትጥቅ ትግልና ድል ቀላል አልነበረም:: ከዚህ በተጨማሪ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይልም ትግሉን ወደፊት ለመውሰድ የጣለው መሰረት በህወሓት መንደር ትልቅ ድንጋጤን ከመፍጠሩም በላይ በህወሓት ላይ ከፈጠረው ጫና የተነሳ ህወሓት ሳይወድ በግዱ የንደራደር ጥያቄንም እንዲያቀርብ ያስገደደው ሁኔታ ገጥሞታል ::

እነዚህ ከላይ ያየናቸው ሁኔታዎችና ሌሎች አሁን ያልጠቀስናቸው ሰፊ የአገራችን ችግሮች በዚሁ በ2013 በመፈጠራቸው ዓመቱ እጅግ አሳዛኝና መራራ አመት ነበር ለማለት ያስችላል :: ለዚህ ሁሉ ችግር ትልቁ ተጠያቂም ህወሓት እራሱ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም  :: 2014 አዲሱ ዓመት ግን ለዓመታት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ ይህ ዘረኛ ቡድን የሚፈጽመውን ግፍ ለማስቆም በጋራ የምንቆምበትና በአገራችን ሁላችንንም በእኩልነት፣ በፍትህ፣ በነጻነት፣ በህግ የበላይነት ሥር ሁላችንም በህግ ፊት እኩል ሆነን የምንኖርባትን አገር ለመመስረትና ለዚህም የህዝብና የአገር ራዕይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለራሱ ሲል አቅሙ በቻለ ሁሉ ትግሉን እንዲቀላቀልና ህወሓትን በመደምሰስ በጋራ ሁላችንንም የምትወድ አገር  ልንመሰርትበት የምንችልበትን መሠረት የምንጥልበት ዓመት ሊሆን  ይገባናል  እላለሁ :: ቸር ይግጠመን ::

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar