mandag 13. januar 2014

የዶ/ር ነጋሶ አስተያየት እና የነጃዋር ፍላጎት


ዛሬ እንዳየሁት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለሎሚ መጽሄት ሰጡ ከተባለው ኢንተርቪው ተመዞ በነጃዋር እየተዘዋወረ ያለ ነገር አለ። ወደተመዘዘው ሃሳብ ትርጓሜ ከመሄዳችን በፊት እነጃዋርን ታሳቢ አድርገውት ሊሆን ስለሚችለው ስትራቴጂ መላምት መስጠት ያስፈልጋል።
በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ላይ ያለቅጥ ስሜት በተጫናቸው የጎሳ ፓለቲካ ተቃዋሚዎች ትችት (ስድብ ቀረሽ ወይንም ስድብ የቀላቀለ ሊሆን ይችላል) በማስነሳት የጎሳ ፓለቲካ ተቃዋሚዎች በታሪካችን ለነበሩ ስህተቶች ምንም አይነት ቦታ አይሰጡም ( ጃዋር እና ጓደኞቹ ሲተረጉሙት ቅዱስ ጦርነት ብለዋል ሊሆን ይችላል) በሚል ፤ ያለፈውንም ሆነ ያሁኑን ችግር ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ የሚፈትሹትን ለዘብተኛ የጎሳ ፓለቲካ አቀንቃኞች የተለየ ሃሳብ መሰንዘር ስትጀምሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ካሚያጋጥማቸው አይነት የትችት ሰይፍ አታመልጡም አይነት ድባብ መፍጠር። እንደ እውነቱ ጃዋር እና ጓደኞቹ እየበጠበጡ ከሚረጩት መርዝ የበለጠ የሚያሳስበው ቁጥራቸው የማይናቅ የጎሳ ፖለቲካ ተቃዋሚዎች በወጣትነት የቁጡነት ስሜትም ሆነ ተፈጥሮአዊ በሆነ ስሜታዊነት በፍጥነት የሚሰጡት መልስ የበለጠ የነጃዋርን ግብ የሚጠቅም መሆኑ ያለመስተዋሉ ነው። ሲሆን እነጃዋርን እንደሌሉ በመቁጠር አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ብቻ በተመጠነ ምክንያታዊ ማብራሪያ በሌላ መልኩ በመስጠት እና ያንን መድረስ ያለበት ቦታ ሁሉ፤ በመድረስ ባለበት መንገድ ሁሉ እያደረሱ እየተደገሰ ያለውን ብጥብጥ ማስቀረት የሚቻልባቸውን ሌሎች ስትራቴጂዎችንም ማሰብ ያስፈልጋል።
ወደ ዶ/ር ነጋሶ ሃሳብ ስመጣ የተናገሩት ነገር ሙሉ ለሙሉ ስህተት አይደለም። የቤተሰባቸውን ታሪክ ነው ያወሩት። ሆኖም ግን የታሪክ ተማሪ እንደመሆናቸው ታሪካዊ አንድምታውን ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው ብየ አስባለሁ። በቤተሰቦቸ ላይ ደረሰ ያሉት ነገር ከሚኒሊክ ፓሊሲ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት እንዳለው በማያሻማ ሁኔታ የሚያመላክት ነገር የለም። የምንሊክ ወታደሮች የወሰዱት እያንዳንዱ ነገር የምንሊክ እውቅና አለው ማለት አይደለም። ቢኖረውም እንኳ ራሱ ጉዳዮ የግድ በጎሳ ፓለቲካ መነጸር መታየት ላይኖርበት ይችላል። አጼ ቴዎድሮስ የኮሶ ሺያጭ ልጂ ብላ የሰደበቻቸውን ንጉሳዊ ቤተሰብ (የራስ አሊ ወገን) ወፍጮ አስፈጭተዋታል። ኮሶ አስጠጥተዋታል። ይሄ ጉዳይ ቀጥተኛ የአጼ ቴዎድሮስ እውቅና እነደነበረው ያመላክታል ታሪኩ። የምንሊክ ያልተገራ ወታደር የወሰደው ርምጃ አጼ ቴዎድሮስ ራሳቸው ወስደዋል ከሚባለው ርምጃ የበለጠ ታሪካዊ ፋይዳ እንዴት ሊኖረው ቻለ? ሁለቱም ድርጊት ትክክል ነው ለማለት አይደለም። የደርግ ወታደሮች መነኩሴ ደፍረዋል እየተባለ ይወራ ነበር። በትክክል የሆነ ነገር ከሆነ ጉዳዮ ከደርግ የወታደራዊ ዘመቻ ፓሊሲ ጋር የሚያገናኘው ነገር አለ? ነው የወታደራዊ ዲሲፕሊን ጉዳይ ነው?የተደፈሩት መነኩሴ ታሪክ እውነት ከሆነ ሊሆን የሚችለው የደርግ ሰራዊት ዘምቶበት በነበረው አካባቢ ነው የሚሆነው። ትግሪኛ ተናጋሪው የኢትዮጵያ ክፍል ሊሆን ይችላል። ደርግ ለትግሪኛ ተናጋሪዎች ያለውን ፖሊሲ ያሳያል ማለት አይደለም። ለመሆኑ መነኩሴዋን ደፋሪው ኦሮሞ ሊሆን የሚችልበት ምንም አጋጣሚ የለም?
ዶ/ር ነጋሶ ከመቶ ዓመት በፊት በቤተሰባቸው ላይ ደረሰ የሚሉትን በወታደሮች (ወታደር ከተባሉ ነው እንግዲህ ) ታስሮ ወፍጮ የመፍጨት ታሪክ በሚተርኩበት በዚህ ወቅት በወያኔ ፖሊሲ በብዙ እስር ቤቶች ውስጥ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ተገልብጠው በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገረፉ ያሉ አሉ ኦሮሞዎችም አማራዎችም አሉ። ጉራጌዎችም አሉ። ትግሬዎችም አይጠፉም። እየተገረፉ ህይወታቸው የጠፋ አሉ። ከአካላዊው ቶርቸር በላይ የመንፈስ ስብራት የሚደርስባቸውም አሉ። በዚህ ሰዓት! የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ፤ ጋዜጠኞች ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች እየደረሰባቸው ያለው ነገር ይሄው ነው።
የ”ራስን እድል በራስ መወሰን” በምንሊክ ዘመን አልኖረም ማለት ራሱ ግራ የሚያጋባ ነው። ታሪካዊ አንድምታን ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ (አናክሮኒስት ) ሊባል የሚችል እይታ ነው። መሰረታዊው ጉዳይ ሌላ ይመስለኛል። ደግመን ደጋግመን ማስታወስ ያለብን ነገር ግጭት እና ቁርሾ የማህበረሰብ አንድ ገጽታ ነው። በታሪክም ነበረ። አሁን ባለንበት ዘመን አለ። ወደፊትም ይኖራል። ይሄ የየትኛውም ማህበረሰብ ገጽታ ነው። እንኳን በማህበረሰብ ውስጥ ይቅር እና በአንድ ቤተሰብ ውስጥ (በአባት እና በእናት በልጆች እና በወላጆች) እስከመገዳደል የሚያደርስ ግጭት ሊከሰት ይችላል። ተከስቷልም። ከኢትዮጵያ እጂግ የከፋ የግጭት ታሪክ የነበራቸው ሃገሮች ያንን የታሪክ ምዕራፍ በጥረታቸው ዘግተው ሌላ የጋራ የስኬት ታሪክ ጽፈዋል።
በማህበረሰብ ውስጥ በማህበራዊም ፤ በኢኮኖሚያዊ ወይንም በፖለቲካ መስተጋብር የሚነሱ ተፈጥሮአዊ ( ኦርጋኒክ ) ግጭቶች በራሳቸው በቂ ናቸው። የእውነተኛ የፖለቲካ እና የፖለቲከኞች ግብ መሆን የሚገባው የሚመስለኝ እነዚያን እያስታረቁ የሚቻቻል ማህበረሰብ በመፍጠር ነጻነት አልባ ያልሆነ እያንዳንዱ ዜጋ እንደችሎታው ከነክብሩ ሰርቶ የሚያድርበት ስርዓት መፍጠር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የተዋለደ የተዛመደ ነው ማለት ማሰብ ከሚቻለው በላይ የመቻቻል እና አብሮ ለመኖር አቅም አለው ማለት ነው። በተለይ ደሞ እንደ ኦሮሞ እና እንደ አማራ የተጋባ የተዋለደ የቋንቋ ተናጋሪ በኢትዮጵያ ያለ አይመስለኝም። ቶሮንቶ ላይ አብሬያቸው ሻይ ቡና ከምላቸው ስምንት ያህል ልጆች አምስቱ (እኔን ጨምሮ) ወይ በአባታቸው ወይ በናታቸው ከኦሮሚኛ የቋንቋ ተናጋሪ የመጡ ናቸው። ወደ አያት ቤት ይገባ ከተባለ ቁጥሩ ሊጨምር ይችላል። ይሄንን ስታትስቲክ ኢትዮጵያ ውሰዱት እና በትልቁ አስቡት።
ማህበረሰብን እንዳልነበረ ለማድረግ የሚያበጣብጥ መርዝ እያመረቱ መርጨቱ የመጨረሻ ግቡ ምንድን ነው ብሎ መጥየቅ ያስፈልጋል። እንዲህ ያለው ድርጊት በአብዮተኝነት ስሜት ሲደረግ ማስተዋል ግራ የሚያጋባ ነው። የግብጽ ሲባል የነበረው “አብዮት” በመጨረሻ አብዮት እንዳልነበረ የግብጽም እንዳልነበረ ገሃድ እየሆነ ይመስላል። ሊቢያ ጭራሽ አሳዛኝ ስርዓት አልባ ማህበረሰብ ሆናለች። ዛሬ እንኳን አንድ ሚኒስተር በታጣቂዎች ተገድሏል። ሊቢያም ውስጥ “አብዮት” ነበር ሲባል ነበር። ዛሬ ካሉበት አጣብቂኝ በምን ተዓምር ሊወጡ ይችላሉ ጥያቄ ነው። አንድ ነገር ግን የተረዱ ይመስላል፤ አብዮተኞች መስለው ጉድ የሰሯቸው እነማን እንደሆኑ የባነኑ ይመስላል።
አረቦች ግን አሁንም ኢትዮጵያን በባላንጣነት የማየት እና የማመሳቀል ፍላጎታቸው የመከነ አይመስለኝም። ግድብ የተባለው ነገር ራሱ መዘዘኛ ሆኗል። ግብጾቹ ባቅማቸው ከኢትዮጵያ ጥቅም ጋር ባላንጣ የሆነ በኢትዮጵያ ላይ ነገር የሚተበትብ አብዮተኛ በባትሪ ከመፈለግ እንደማይመለሱ ሳስብ ፤ አረቦቹ ለነጃዋር የ ጎሳ ”አብዮተኛ” ቡድን በርግጥ የሜዲያ ሽፋን ብቻ ነው የሚሰጡት ወይንስ በሌላ መልኩም እያገዟቸው ነው የሚለው ለኔ ጥያቄ ነው። ደጋፊያቸውም ተቃዋሚያቸውም በስሜት ከመነዳት እና ስስ ስሜቱን ከማስነካካት ቆም ብሎ በጋራ በዘዴ ማሰብ ያለበት ይመስለኛል።
እናም ዶ/ር ነጋሶ ላይ ሊያስነሱ ያሰቡት አጥፊ አቧራ የሚገባውን ግምት መሰጠት አለበት። ዶ/ር ነጋሶ በራሳቸው ሚዛን ሚንሊክን ተቹ እንጂ ያለፈውን ታሪክ ሁሉ ሰብስበው ወደ ቆሻሻ አልጣሉትም። በዚህ አጋጣሚ አንዳንድ የኢትዮጵያ የህትመት ሜዲያዎች አንገብጋቢ የሆነና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ፓለቲካዊ ጉዳይን እንዳልባሌ ነገር ( ሆነ ተብሎም ይሆናል) እንደ ፓፓራትዚ የሚያስተናግዱበት አገባብ እየፈጠረ ያለውን ችግር ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው።
ተቀባዮም እንደዛው። ለኢትዮጵያ የተደገሰው ነገር አሳሳቢ ነው። ወያኔ መሪ ተዋናይ ነው። ቆየት ያለውን ረስተን ሰሞኑን በሱዳን በኩል እያደረገ ያለውን ነገር ሰምተናል። ሶማሊያ ላይ ያዝረከረከውን ነገር እናውቃለን። በዚህ ላይ በዓረቦች ድጋፍ እየተቀጣጠለ ያለ የሚመስል ነገር ፤ የጎሳ ፖለቲካውን የጀርባ አጥንት የሚጨምርለት መስሎት ወያኔ ከፍሎ ባሰማራቸው ሰዎች አማካኝነት የነጃዋርን ቡድና ማቆላመጥ ይዟል። እየተስተዋለ!

ድሜጥሮስ ብርቁ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar