søndag 26. januar 2014

የብሔር ፖለቲካ አሳፋሪ ነው፡፡


አንድነታችንን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ብናተኩር ሁላችንንም ይጠቅመናል፡፡ 

ኢትዮጵያ ምሳሌ ልትሆንበት የምትችልበት ነገር ሃይማኖት ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን በውስጧ አቅፋ የያዘች አገር ናት፡፡ አይደለም ሰማንያ ቀርቶ ሁለት ብሔረሰቦች ያሉባቸው አገሮች ግጭት ውስጥ ሲገቡ እናያለን፡፡ 

ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃቅን ግጭቶች የሉም ማለት ባንችልም፣ በአጠቃላይ ግን ለመኖር የሚያዳግት ግጭት ግን አስተናግዳ አታውቅም፡፡ ይህ ታሪካችን የሚያኮራን ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን የሚስተዋሉት ነገሮች ሃይ ሊባሉ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ስለአብሮ መኖር ታሪካችን የማንጠነቀቅለት ከሆነ ይህ አኩሪ ታሪክ ሊበላሽና ሊጠፋ ይችላል፡፡

በተለያዩ ወቅቶች በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚነሱ የብሔር ግጭቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት ሊያሳዩን ይችላሉ፡፡ በተለይም አገሪቱ ተስፋ የምታደርግባቸው እነዚህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠባብ በሆነ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ገብተው ሲጋጩና ሲበጣበጡ ማየት አሳፋሪ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአማራ ብቻ አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ብቻም አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የደቡብ ብቻም አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የትግራይ ብቻም አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የሁሉም ናት፡፡ ስለዚህ አንዱ ብሔር ከአንዱ ብሔር አይበልጥም፡፡ አንዱ ብሔር ከአንዱ ብሔርም አያንስም፡፡ ሁሉም እኩል ነው፡፡ አንዱ ከአንዱ ይሻላል በሚል ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲካ አንድነታችንን ማፍረስ አይገባንም፡፡ የሁሉም ብሔሮች መገኛ የሆነችውን ኢትዮጵያን መመልከት ይገባል፡፡ በዚህም ረገድ ራሳችንን መሳል ተገቢ ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን በየጊዜው እየዶለዶምን ሄደን አንድነታችንን ልናጣው እንችላለን፡፡

ሃይማኖቶች በመርህ ደረጃ አይጋጩም፡፡ ሁሉም ፍቅርን፣ መተሳሰብንና ሰላምን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁሉም የመረጠውን ሃይማኖት የመከተል መብት አለው፡፡ ነገር ግን የአንድ ሃይማኖት ጠበቃ ነኝ በሚል የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ማድረግ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው፡፡ ሰዎች በሚከተሉት ሃይማኖትና በማንነታቸው ፈጽሞ ሊፈረጁ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ከሁሉም በላይ ሰውነታቸው ይበልጣልና፡፡ 


ስለዚህ ሰዎች ሐሳባቸውን በማንፀባረቃቸው ምክንያት በጠላትነት ሊፈረጁ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሕገ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊም ነውና፡፡ ጽንፈኛ የሆነ አመለካከት በመያዝ የእኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክል ማለት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኋላቀር የሆነ ብቻ ሳይሆን የማያስኬድ ነው፡፡ ስለዚህ ራስን በአንድ ሳጥን ውስጥ ጨምሮ እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን ማለት አንድነታችንን ሸርሽሮ በኋላ ባዶ ሊያስቀረን ይችላል፡፡ 

በመሆኑም በሃይማኖቱም ሆነ በፖለቲካው እንዲሁም በሌላውም ጉዳይ የእኔ ሐሳብ ብቻ ይንገሥ ማለት ማንንም የትም አያደርስም፡፡ ስለዚህ በየትኛውም ጉዳይ ላይ ጽንፈኝነትን በማስወገድ አንድነታችንን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ብናተኩር ሁላችንንም ይጠቅመናል ፡፡


 ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar