ኢቴቪ ጠፍቷል ያለውን የአኬልዳማ ዶክመንተሪ ፊልም ሙሉ ቅጂ አቀረበ
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር የሆነው አንዷለም አራጌና የብሄራዊ ምክር ቤት አባል ናትናኤል መኮንን በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ እነ አንዷለምን የያዝነው በቂ ማስረጃ ሰብስበን ነው ሲሉ ከቆዩ በኌላ የኢትዩጵያ ቴሌቪዥን ‹‹አኬልዳማ››የተባለ ዶክመንተሪ ፊልም በማስረጃ መልክ ለእይታ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡
በፊልሙ የአንድነት የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ የሆነው አንዷለም አራጌ ከግንቦት ሰባት ጋር ግኑኝነት እንዳለው በማስመሰል ከመቅረቡም በላይ የአንድነት አባላት ያልነበሩ በደረቅ ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦችን የፓርቲያችን አባላት መሆናቸውን እንዲመሰክሩ ተደርገዋል፡፡
በህጋዊ መንገድ ፓርቲያችን ከህዝብ ጋር ለመወያየት በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የጥናት ጽሁፍ አቅራቢነት አዘጋጅቶት የነበረውን ውይይት በህቡዕ የተዘጋጀ በማስመሰል በፊልሙ ለክስ በሚመች መልኩ መቅረቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስረጃ አሰባስበን ነው የያዝናቸው ማለታቸውን ትዝብት ውስጥ የከተተ ነበር፡፡
አኬልዳማ ፊልም ለህዝቡ በቀረበበት ወቅት በፍርድ ቤት ጉዳያቸው መታየት ያልጀመረን ተጠርጣሪዎች ሽብርተኞች በማለት መፈረጁና በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሰውን ፓርቲያችንን ጭምር ‹‹የግንቦት ሰባት ጉዳይ አስፈጻሚና የሽብርተኞች ተላላኪ››በማለት መፈረጁም አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ የጣብያው ሃላፊዎች እርምት እንዲያደርጉና በአንድነት ፓርቲ የተዘጋጀን ፊልም ለህዝብ እንዲያሳዩ በደብዳቤ ጭምር ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ፓርቲያችን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ተገድዷል፡፡
ጉዳዩን በ2004 ወርሃ ታህሳስ መመልከት የጀመረው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ልደታ የፍትሃ ብሔር ምድብ ችሎት መዝገቡን ለ15 ጊዜያት ከሳሽና ተከሳሽን ሲያከራክር ከቆየ በኋላ ለታህሳስ 11/2006 ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ይዟል፡፡ከትናንቱ ቀጠሮ ቀደም ብሎ የኢቴቪው ጠበቃ አኬልዳማ የተባለው ዶክመንተሪ ፊልም መጥፋቱን እንዲሁም የዶክመንተሪው ሃላፊ የነበሩት ግለሰብ ወደ ውጪ አገር በመሄዳቸው የተነሳ ቅጂውን ለማቅረብ ደምበኞቹ መቸገራቸውን ገልጾ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ዶክመንተሪውን የግዴታ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው በማዘዛቸው በተለዋጭ ቀጠሮ ቅጂውን ይዘው ቀርበዋል፡፡
የአንድነት ጠበቃ ተከሳሽ ያቀረቡትን ፊልም ቅጂ ለማመሳከር እንዲሰጣቸው ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ይህንን ማዘዝ እንደማይችል በመጥቀስ ለውሳኔ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የአንድነት ጠበቃ ተከሳሽ ያቀረቡትን ፊልም ቅጂ ለማመሳከር እንዲሰጣቸው ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ይህንን ማዘዝ እንደማይችል በመጥቀስ ለውሳኔ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ከዳዊት ሰለሞን
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar