የኢትዮጵያን መንግስት ለፍርድ ለማቅረብ ከተነሱት ስዊድናዊ ጠበቃ ጋር ውይይት ተደረገ
ቅዳሜ ኖቬምበር 2 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ መድረክ በስዊድን የወያኔን መንግስት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የተጀመረውን ክስ መነሻ በማድረግ የክሱን ሂደት ከሚመሩት ከስዊድናዊው ጠበቃ ከስቴላ ያርዴና ከሌሎች እንግዶች ጋር በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ወይይት አደረገ።
ውይይቱ ከቀኑ 14፡00 ሰዓት የተጀመረ ሲሆን ውይይቱን የከፈቱት የመድረኩ ሊቀ መንበር ም/ኢኒስፔክተር ሚሊዮን ብሩ ናቸው። ኢኒስፔክተር ሚሊዮን በንግግራቸው መክፈቻ ጥሪ የተደረገላቸውን እንግዶችና ተሰብሳቢውን ህዝብ አመስግነው መድረኩ የተቋቋመበት ዓላማ በሀገር ውስጥና በውጪ የሚደረገውን የነጻነት ትግል የተደራጀ መልክ ይዞ የሚጓዝበት መንገድ ለማመቻቸትና በየጊዜውም ይህንን መሰል ውይይት በማድረግ ትግሉን ለመርዳት መሆኑን ገልጸው የዛሬውንም ስብሰባ የዚህ መነሻ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ከሳቸው በመቀጠል መድረኩን እንዲመሩ የተጋበዙት ጋዜጠኛ ወንድማገኝ ጋሹ፤ ዶ/ር ሙሉዓለም አዳምን የመጀመሪያው ተናጋሪ አድርገው ጋብዘዋል። ዶ/ር ሙሉዓለም የመድረኩን አዘጋጆች አመስግነው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአስከፊ ሁኔታ ላይ መውደቁን ሙስናውም እያደረ መባባሱን የመንግስት ባለስልጣኖች ወደ ውጪ የሚያሸሹት ገንዘብ እየናረ መሄዱን ገልጸዋል።
እንዲሁም የዘር ፖለቲካ እየተስፋፋ መሄዱን፣ የስለላ መዋቅሩም መጠናከሩንና ህዝቡን መግቢያ መውጫ ማሳጣቱን ከዚያም አልፎ በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድረስ መዝለቁን አስረድተዋል። የወቅቱን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርንም ንግግር በመጥቀስ በሰላማዊ ሁኔታ የሚደረገው ትግል አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደወደቀ አመላክተዋል።
ሁለተኛው ተናጋሪ የመድረክ መሪው ጋዜጠኛ ወንድማገኝ ጋሹ ሲሆኑ እርሳቸውም በሀገራችን ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሰው ልጅን የሰውነት ደረጃ ያቃለለ፣ ሙሉ ለሙሉ ያዋረደና መብት የገፈፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለሃያ ደቂቃ የቆየ ይህንኑ የሚያመላክት ፊልም አሳይተዋል።
ቀጥሎም የተነሱበትን አላማ እንዲያስረዱ በጉጉት ይጠበቁ የነበሩት ስዊድናዊው ጠበቃ ስቴላ ያርዴ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል። ጠበቃ ስቴላ ያርዴ የስዊድን ቴሌቪዥን ባሳየው ዘጋቢ ፍልም ስሚታቸው እንደተነካ ገልጸው ይሄንን አሰቃቂ ወንጀል የፈጸመውን የወያኔን መንግስት ለፍርድ ለማቅረብ እንደተነሱ አስረድተዋል።
በፊልሙ ላይ የታዩት የወንጀል ድርጊቶች ለተነሳንበት ክስ አሳማኝ መረጃ ከመሆኑም በላይ በተለይ በእስር ላይ ያሉ ስዎችን የመድፈርና የማስወለድ ድርጊት ወንጀሉን የሚያከብደው ሲሆን በቅርባችን ባሉት ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ላይም የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በደል ክሱን እንደሚያጠናክርው ገልጸዋል።
ሁኔታውን ሲያብራሩም አሁን ያሉንን መረጃዎች ይዘን ለሚመለከተው አካል አመልክተናል። ወደ ቀጣዩ እርምጃ ለማለፍ የነሱን ውሳኔ መጠበቅ ይኖርብናል። የስዊድን ፖሊስም ለዚህ ጉዳይ ትብብሩን አልነፈገንም ብለዋል።
ከተሰብሳቢው ህዝብም ክሳችሁ ትኩረት ይዞ የተነሳው በኦጋዴን በታየው በደል ብቻ ነው ወይስ በሌሎችም ክልሎች የተፈጸመውን አጠቃሎ ይይዛል? ለተባሉት ሲመልሱ በሌሎች ክልሎች የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድርጊቱን በሚያስረዳ መልክ ማስረጃ አሰባስበን መያዝ የመጀመሪያ ስራችን ይሆናል ብለዋል።
ማስረጃ ልንሰጣችሁ ብንፈልግ በምን መልኩ ማቅረብ እንችላለን ለተባለው ጥያቄ ደግሞ ሲመልሱ ማስረጃ ለመስጠት በተናጠል እኔን ማግኘት አያስፈልጋችሁም ከተለያየ ሰውና ቦታ የምታገኙትን መረጃ ይህንን የሚያሰባስብ የመረጃ ቡድን አቋቁማችሁ ቡድኑ መረጃዎችን አጣርቶና አሰባስቦ ቢሰጠን የተሻለ ይሆናል ብለዋል።
በስብሰባው ላይ የተገኙት የአፋር ህዝብ ብሄራዊ ክልል የሰብዓዊ መብት ተወካይ በበኩላቸው በአፋር ህዝብ ላይ እየተደረገ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሌላው ክልል የማይተናነስ መሆኑን ገልጸው በእጃቸው የሚገኘውን መረጃ ለጠበቃ ስቴላ ያርዴ ሰጥተዋል።
የመጨረሻው ተናጋሪ መቶ አለቃ አበረ አዳሙ ሲሆኑ እርሳቸውም ‹‹ድርጅታዊ ዘረኝነት›› በሚል ርዕስ የተሰብሳቢውን ህዝብ ስሜት የሳበ ንግግር አድርገዋል። በዚሁ ንግግራቸው እንዳብራሩት የኢትዮጵያ መንግስት የድርጅታዊ ዘረኛነትን አገዛዝ አጥብቆ ለመያዝ የክልልና የፌዴራል ፖሊስን፣ የደህንንነት መምሪያውን፣ የመከላከያ ሰራዊቱን፣ የስራ ፈጻሚ ክፍሎች እንዲሁም የገንዘብ ገቢ የሚያስገኙ ተቋማትን በአንድ ዘር በማደራጀት ሃላፊዎች መድቦ ምንም አይነት ቀዳዳ ሳይከፍት ሁሉን ነገር ከቁጥጥሩ ስር በማድረግ
ድርጅታዊ ዘረኝነቱን ለማጠናከር ችሏል ብለዋል።
በመሆኑም ተቃዋሚ የሆንን ሁሉ ይህንን ድርጅታዊ ዘረኝነት አውቀን ትግላችንን ማጠናከር ይገባናል ለዚህም የሚያገለግለን መተባበርና እርስ በርሳችን መተሳሰር ሲሆን ይህን የአፈና መዋቅርም ማፍረስ የምንችለው በተጠናከረ የአንድነት ትግል ብቻ ነው በማለት ሰፊ ማብራርያ ሰጥተዋል። የመቶ አለቃ አበረ ንግግር በብዙዎች ታዳሚዎች ዘንድ ለለውጥ የሚያነሳሳ ስሜት ፈጥሮ ነበር። በመጨረሻም የውይይት መድረኩ ለወደፊትም ከልዩ ልዩ እንግዶች ጋር በዚህ መልክ ወይይቶች እንደሚደረግ ገልጾ ውይይቱ 18፤00 ስዓት ላይ ተጠናቋል። (ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የተጠናቀረው ዘገባ ወለላዬ ከስዊድን)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar