እንጀራ ብሔራዊ ደረጃ ወጣለት
አንዳንዴ ለገበያ የሚቀርበው እንጀራ ለበሽታ የሚዳርግ ነው
የጤፍ እንጀራ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ብሔራዊ ደረጃ እንደወጣለት ታወቀ። ፋና ኤጀንሲውን በመጥቀስ እንዳመለከተው ጤፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ደረጃ ወጥቶለት መጽደቁን አመልክቷል። ዜናው ደረጃ የወጣለት ጤፍ ምን መስፈርቶች እንደተቀመጡለት አላብራራም። በኢትዮጵያ የጤፍ እንጀራ ወደ ውጪ በመላክ ንግድ የከበሩ ነጋዴዎች በብሔራዊ ደረጃ በጸደቀው አዲሱ የጤፍ ደረጃ መሰረት አዘጋጅተው ኤክስፖርት መላክ እንዳለባቸው የሚያስገድድ ሁኔታ ስለመቀመጡም የተገለጸ ነገር የለም።
በአውሮፓና አሜሪካ በተለያዩ ሱፐር ማርኬቶች፣ የግል የገበያ ሱቆችና የቤንዚን ማደያዎች ገበያ ላይ የሚገኘው የጤፍ እንጀራ አንዳንድ ጊዜ ደረጃውን ያልጠበቀ፣ የሚኮመጥጥ፣ አይን የሌለው፣ የሚፈረካከስና ወዝ የሌለው እንጀራ የሚቀርብበት አጋጣሚ በርካታ ነው። በላስቲክ ታሽጎ ከፍሪጅ እየወጣ የሚሸጠው እንጀራ ጉዱ የሚታወቀው ቤት ከገባ በኋላ በመሆኑ በርካታ ተጠቃሚዎች እንደሚማረሩ ለማወቅ ችለናል።
አንድ እንጀራ እስከ ሰባ ብር በመግዛት የሚመገቡ የስካንዲቪያን አገራት ነዋሪዎች እንጀራ መመገብ ቢወዱም ገበያው ላይ አንዳንዴ የሚቀርበው እንጀራ ለጨጓራ ችግር የሚዳርግ እንደሆነ ተናግረዋል። አዲስ ብሔራዊ ደረጃ ያወጣው ኤጀንሲ ህግ ማውጣቱን ብቻ ሳይሆን በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። እንጀራ ወደ ውጪ ለመላክ ፈቃድ ያወጡ ነጋዴዎች ህጉን አክብረው እንዲሰሩ የማስገደድ ተግባሩን እንዲገፋበትም ጠቁመዋል። ችግር ካጋጠማቸውም ማስረጃ በመያዝ ቅሬታቸውን ማሳወቅ የሚችሉበት አግባብ እንዲዘረጋላቸው ሃሳብ ያቀረቡም አሉ።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar