mandag 1. juli 2013

አልሸባብ በሶማሊያ ተሽመደመደ፤ ሼኽ ዳሒር ሃዌስ ተይዘዋል፤
አሸባሪነትን በመዋጋት ሲሞዳሞዱ የቆዩት ኢትዮጵያና አሜሪካ ወዴት ያመሩ ይሆን?
SOMALIA MILITIA
የአልሸባብ መሪዎች በራሳቸው ተዋጊዎች መገደላቸው ተሰማ። ከተገደሉት መካከል አንደኛው ያሉበትን ለጠቆመና ላጋለጠ አምስት ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ እንደሚሰጥ የታወጀባቸው ነበር። የቪኦኤ የአማርኛው ክፍል በዘገበው ዜና መሰረት አልሸባብ በሶማሊያ እየተንኮታኮተ የመክሰም ደረጃ ላይ መድረሱን አመላካች ይመስላል።
አብዱልአዚዝ አቡ ሙስ አብ ባሠራጨው የድምፅ መልዕክት የሙጃሕዲኑ ታጣቂዎች በመካከላቸው መከፋፈልን ለመፍጠር ይጥሩ በነበሩ አባሎቻቸው ላይ ዘመቻ ካካሄዱ በኋላ የተወሰኑትን በቁጥጥር  ሲያውል፣ እጅ ለመስጠት አሻፈረኝ ያሉ ነበሩ ብሏል። “ሁለቱ እጃቸውን እንዲሰጡ ሲጠየቁ አሻፈረን ብለው አንገራገሩ፣ በተኩስ መካከል ተገደሉ፤ አምላክ ነፍሳቸውን ይማርና በገነት ያስቀምጥ፡፡ ሃሣቡ እነርሱን ለመግደል አልነበረም፡፡ በቁጥጥር ሥር አውለን እሥልምና ችሎት ፊት ልናቀርባቸው ነበር” ሲል እስልምና ችሎት ፊት ሳይቀርቡ በተኩስ ልውውጡ ወቅት መገደላቸው እንዳሳዘነው መግለጹን የቪኦኤ ዜና ያስረዳል።
ሰዎቹ የተገደሉት ከሞቃዲሾ 350 ኪ.ሜ በስተደቡብ በምትገኝ ብራቫ የምትባል ከተማ ውስጥ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የተገደሉት ሰዎች እነማን እንደሆኑ የአል-ሻባብ ቃል አቀባይ አልተናገረም፡፡ ይሁን እንጁ የቪኦኤ ሶማሊኛ አገልግሎት የተለያዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን አነጋግሮ በተለያዩ ስም የሚጠሩት የአልሸባብ አመራር መሞታቸውን አመልክቷል። በዚሁ መሰረት ኢብራሂም ሃጂ ጃማ ፣ ኢብራሂም አል-አፍጋን ፣ በተቀጥያ መጠሪያው አቡ ባካር አል-ዛይሊዪ እና ሼኽ አብዲሃሚድ ሃሺ ኦልሃዬ ወይም በቅፅል ስም ሞዐሊም ቡርሃን የተገደሉ መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡
መሪዎቹ የተገደሉት የዛሬ አሥር ቀን ሰኔ 12 መሆኑንም የቪኦኤ ምንጮችን የጠቀሰው የሶማሊኛ አገልግሎት ዘገባ አመልክቷል፡፡የአል-ሻባብ ምንጮች እንደሚሉት አል-አፍጋን የተገደለው ከመስጂስ እየወጣ ሳለ በተተኮሰበት ተከታታይ ጥይት ሲሆን ሙዐሊም ቡርሃን የተገደለው ከቤቱ ተይዞ ከተወሰደ በኋላ ነው፡፡
ይህ አጋጣሚ ከተፈጠረ ከሁለት ቀናት በኋላ ለተገደሉት ሁለት ሰዎች የቅርብ ወዳጅ እንደነበረ የሚነገረው ዋነኛው የአል-ሻባብ መሪ ሼኽ ሐሰን ዳሂር አዌይስ ከአካባቢው በጀልባ በማምለጥ ማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ ተይዞ እጁ ለመንግሥት አስረክቧል። ከተገደሉት አንዱ ኢብራሂም አል-አፍጋን በአል-ሻባብ ውስጥ በርካታ የሥልጣን ቦታዎች የነበሩት ሲሆን የቡድኑ ምክትል መሪ፣ የገንዘብ መምሪያው ኃላፊና የኪስማዮ ገዥ ሆኖ ሠርቷል፡፡ ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ ያሉበትን መረጃ ለሚሰጥ በእያንዳንዳቸው ራስ የአምስት ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ እንደምትሰጥ ዩናይትድ ስቴትስ ማስታወቂያ ካወጣችባቸው ሰባት የአል-ሻባብ መሪዎች አል-አፍጋን አንዱ ነው፡፡
አል-አፍጋን ዩናይትድ ስቴትስ፣ ቨርጂንያ ውስጥ ይኖር የነበረ ሲሆን እአአ በ1980ዎቹ ውስጥ ከሙጃሕዲን ጎን ተሰልፎ ለመዋጋት ወደ አፍጋኒስታን መሄዱንና በ1991 ዓ.ም የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ሲወድቅና ሥርዓተ-መንግሥቱ ሲፈራርስ እጅግ የከፋ ዓይነት ጂሃድ ወደ ሶማሊያ ማስገባቱና ሶማሊያ ውስጥ የመጀመሪያውን የጂሃድ ማሠልጠኛ ሠፈር ማቋቋሙን ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡
አል-አፍጋን ከአል-ቃይዳው መሥራችና መሪ ኦሣማ ቢን ላደን ጋርም ብዙ ግንኙነቶች እና ንግግሮች እንደነበሩት ቢን ላደን በ2011 ዓ.ም ከተገደለ በኋላ ሲናገር ድምጹ ይሰማ እንደነበር ታውቋል፡፡ ሌላው ተገዳይ ሙአሊም ቡርሃን አል-ሻባብ ውስጥ ዋነኛ የሚባል የሃይማኖት ሊቅ እና የቡድኑ የመማክርት ምክር ቤት አባል እንደነበረ ተገልጿል፡፡
የአልሻባብ አመራር በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲዳከም፤ ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢህአዴግ የአሜሪካ ወዳጅ ነኝ በማለት እንዲሁም አሜሪካም “ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሸሪካችን ነች” በማለት ሲሞዳሞዱበት የነበረው አጀንዳ “በቀጣናው አሸባሪዎችን መዋጋት የሚል ነበር”፡፡ በተለይም እነ አቶ መለስ አልሻባብ የአልቃይዳ ስሪት ነው፤ አሸባሪነትን እንዋጋለን በማለት በአልሻባብ ስም የፈለጉትን የፖለቲካ ጥቅም ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ ታዲያ ይህ የአልሻባብ መዳከም በዕቅድ የተከናወነ ይሆን? ወይስ የተበላበት ዕቁብ ስለሆነ ሌላ የታሰበ አዲስ ፕሮጄክት አለ? አልሻባብ ቁጥር 2 ወይም “ጸረ አሸባሪነትን መዋጋት ቁጥር 2”? ወይስ ፕሬዚዳንት ኦባማ በአፍሪካ ጉብኝታቸው ከምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን አለመምረጣቸው ጋር ተዳምሮ አሜሪካ ለምስራቅ አፍሪካ ድራማ አዲስ የፖለቲካ ጽፈ ተውኔት አዘጋጅታ ይሆን? መቆየት ደጉ ብዙ ያሳየናል!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar