አበባ እርሻ የሚሰሩ የኬሚካል ጉዳተኞች በርክተዋል
የውጪ ምንዛሬ ገቢው 40% ቀነሰ
በከፍተኛ ደረጃ የእርሻ መሬቶችን ወደ አበባ እርሻ ማሳ ለሚቀይሩ ባለሃብቶች በመሸጡ ተቃውሞ የሚሰነዘርበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ የዜጎችን ህይወት እየተፈታተነ ነው። በአነስተኛ ክፍያ በአበባ እርሻዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ወገኖች ከኬሚካል ጋር በተያያዘ እየደረሰባቸው ያለው የጤና መጓደል አስጊ እንደሆነ አሁንም ድረስ ትኩረት እንደሚፈልግ እየተነገረ ነው።
ለገቢው ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መንግስት በበጀት ዓመቱ ከዘርፉ የጠበቀውን ገቢ አለመግኘቱን ተጠቁሟል። ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ የአበባ ዘንግ፣ 114ሺ ቶን አትክልት እና 13ሺ ቶን ፍራፍሬ ባለፉት 11 ወራት ወደ ተለያዩ ሀገራት ቢላክም መጠኑ ከእቅድ በታች እንደሆነ ተገልጾዋል። ፋና የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጄንሲን ጠቅሶ እንደዘገበው ወደ ውጪ ከተላኩት የአትክልት ምርቶች ከ212 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። ገቢው ከእቅዱ ስልሳ በመቶ ብቻ ነው። ኤጀንሲው ለገቢው መቀነስ የአለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር ሁኔታ መለዋወጥ እንደ ምክንያት አቅርቧል።
ከአበባ እርሻ ጋር በተያያዘ በርካታ ዜጎች ለበሽታ መዳረጋቸውና በቂ የጤና ዋስትና እንደሌላቸው በተደጋጋሚ የሚገለጽ ችግር ነው። በአበባ ማበልጸጊያ ድንኳን ውስጥ የሚሰሩ ዜጎች ለኬሚካል ብክለት መጋለጣቸው የከፋ ችግር ከመሆኑም በላይ ከእርሻዎቹ የሚወጡ ፍሳሾች ወራጅ ውሃና ወንዝ ጋር በመቀላቀል አደጋ እያስከተለ ነው። ከዚህም በላይ የአበባ እርሻዎች ከፍተኛ ሃይል ያለው መርዝ ስለሚጠቀሙ መሬቱ ለወደፊቱ እህል እንደማያበቅል ባለሙያዎች በጥናት አረጋግጠው ያቀረቡበት የማይመከር ኢንቨስትመንት እንደሆነ መጠቆሙ አይዘነጋም።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar