søndag 27. mars 2016

ከብሄር በፊት ሀገር!!!

ከብሄር በፊት ሀገር!!!

በሀገራችና በህዝባችን ህወሓት ከሚፈፅማቸው ግፍና በደል በተጨማሪ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ሁኔታ የብሄርተኝነትን መርዝ አሰራጭቶል እያሰራጨም ይገኛል። ይህንም ያደረገበት ዋነኛ ምክንያት የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ሆን ብሎ ያደረገው ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱ የሆነ ብሄር እንዳለሁ ሁሉ ሰው ብሄርተኝነቱን እራሱ ፈልጎት የመጣ ነገር አይደለም፤ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው። ስለዚህ ህወሓት አሁን ላይ ስልጣኑን ለማራዘም ብሎ ብሄርን ከብሄር ማናከስ ትልቁ ስራው አድርጎታል፤ እያናከሰም ይገኛል። እስከመቼ በብሄር ፖለቲካ እያጫወተን እንዘልቀዋልን። ህወሓት ገና ጫካ እያለ አላማ አድርጎ የተነሳው የህዝቦችን አንድነት የመበጣጠስ አላማ አድርጎ የተነሳ ቡድን ነው።

አሁን ላይ በሀገራችን ያለው ስልጣን የአንድ ብሄር ስልጣን ነው። ይህ የአንድ ብሄር ስልጣን ለ25 አመታት በኢትዮጵያና በህዝቦቾ ታሪክ ግፍና በደል እንዲፈፀም አድርጓል። ህወሓት ብሄር ተደራጅቶ በሀገርና በህዝብ ላይ ይህ ነው የማይባል ኢፍትሃዊ ግፍና በደል ፈፅሟል፤ እየፈፀመም ይገኛል። መቼም አሁን አሁን እየተፈፀመ ያለው ግፍና በደል በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ይህም የሆነበት ምክንያት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በዜጎች ላይ የተወሰደው እኩይ ተግባር ይህ ነው የሚባል አይደለም።

የአንድ ብሄር ስልጣን ላይ መቀመጥ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ግፍና በደሎች ሰሚ አካል የላቸውም። ምክንያቱም ሀገሪቱና ህዝቦቾን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር አድርገውታል። ህግ አውጪ እነሱ፣ ህግ ተርጓሚ እነሱ፣ ህግ አስፈፃሚ እነሱ ይህ ሁኔታ ባለበት ሀገር ላይ የዜጎች የመኖር ዋስትና አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛሉ። ይህን የፈጠረው የአንድ ብሄር ስልጣን ስለሆነ በህዝባቸው የሚፈፀምባቸውን በደል ወይም ግፍ ለመቃወም የብሄር ትግል እንዲያስቡ ያስገድዳቸዋል። ነገር ግን የብሄር ትግሉ መደረጉ ባይጠላም፤ ሀገራዊ ትግል እንዲሆን መፈጠሩ ሁሉምንም ብሄር ያካተተ ያደርገዋል።

ህወሓት ሲታገል የነበርው አንድን ብሄር ነፃ ለማውጣት ታግሎ፤ አንድን ብሄር ለስልጣን አብቅቷል። ይህ ስርዓት አብዛኛውን ብሄር ብሄረሰብ  ጎድቶታል እየጎዳውም ነው። አንዳንቺን ለአንዳንቺን እንዳንያያዝ፣ እንዳንግባባ፣ እንዳንሰማማ፣ እንዳንተማመን…………….. ያደረገ ስርዓት ነው። የአንድ ብሄር ስልጣን የፈጠርውን ችግር እያየን የብሄር ትግል ውስጥ የገባን ልብ ብለን ልንገነዘብ ይገባናል። "አንድ ተረት አለ እሳትን ያየ በአመድ አይስቅም!!"

ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ሀገር ናት። እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ የራሱ የሆን ቋንቋና ባህል ወግ አለው። ለዘመናት ተከባብሮና ተፋቅሮ የኖረ ማህበረሰብ ነው። አሁን አሁን ህወሓት በፈጠረው ስርዓት ብሄር ከብሄር ጋር ሲያስማማ ወይም ሲያከባብር አልተስተዋለም። ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት በሀገሪቱ የአንድ ብሄር ስልጣን ዘመን እንዲራዘም ሆን ተብሎ የሚደረግ ድርጊት ነው።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዚህ ሶሻል ሚዲያ ላይ የሚስተዋሉ ነገሮች አሉ። እነዚሁ ነገሮች ብሄር እና ሀገር እየታገልን ያለነው ስለብሄር ነው ወይስ ስለሀገር የሚለውን ነገር እንድመለከት አድርጎኛል። ሁላችንም የእኔ የምንለው ብሄር አለን። እንዱሁም ሁላችንም በአንድ ስም ሊያስጠራን የሚችል ሀገርም አለን!! ታዲያ ትግላችን ከሀገር ወደ ብሄር እየሄደ ይመስላል።  አንድ ብሄር ብቻውን ህወሓት ተቃውሞ ከስልጣን ያስወግዳል የሚል እምነት የለኝም። ባይሆን ሁሉም በተቃውሞ ቢሳተፍ አንድ ደረጃ ላይ እንደርስ ነበር። እርግጥ ነው በብሄራችን ላይ የሚፈፀሙ ግፍና በደሎች ስለብሄራችን እንድንቆም ያደርጉናል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ተቃውሞ የለኝም። ነገር ግን እየሆነ ያለው ሁሉም   ስለእራሱ ብሄሩ የሚታገል ከሆነ ስለሀገራዊ ትግል እንዴት ልናስብ እንችላለን። እዚህ ጋር ቆም ብለን እናስብ!!  

ከብሄር በፊት ሀገር!! ሀገር እየፈረሰ ብሄር ይኖራል ማለት ዘበት ነው!! ይህ ደግሞ ማንም ሰው ሊያውቀውና ሊገነዘበው ግድ ይላል። ሀገርን ውስጥ ብዙ ህዝቦች አሉ!! አሁን ላይ ህወሓት ሀገርና ህዝብ እያጠፋ የሚገኝበት ሰዓት ላይ ነን ፤ይህ ደግሞ ከማንም የተደበቀ አይደለም። እርግጥ ነው ህወሓትና ቤተሰቦቻቸው ይህን እውነታ አይቀበሉትም። ምክንያቱ አላማ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ያሉት በሀገሪቱ ህዝብ ንብረትና ሀብት ላይ ስለሆን በህወሓት ላይ ምንም አይነት ተቃውሞ መስማትም ሆን ማየት አይፈልጉም።

ስለሆነም የምናደርገው ትግል ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች  ያማከለ መሆን አለበት ለጋምቤላው ህዝብ ኦሮሞው ካልጮህለት፣ ለኮንሶ ህዝብ አማራው ካልጮህለት፣ ለሀረሪ ህዝብ ትግሬው ካልጮህለት. . . . . . . . ጩህታችን ለመላው ለህዝባችን ካላደረግነው ተመልሶ እንደ ህወሓት አይነት ስርዓት መገንባቱ የማይቀር ነው።  ህወሓት ግፍና በደል መላው ህዝባችን ላይ ነው። ድምፅ ለሌላቸው ህዝቦች ድምፅ መሆን ካልቻልን አሁንም ይህ ፋሺስት ስርዓት በሀገሪቱና በህዝቡ ላይ የሚያደረሰውን መከራ ይቀጥላል። ይህ እንዳይሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከብሄር በፊት ለሀገሩና ለመላው ህዝብ  መቆም አለበት!! ሀገር ሲኖር ብሄር ይኖራል። አንድ ብሄር ሀገር መሆን አይችልም!! ሀገር ግን የብዙ ብሄር ብሄረሰብ ናት!!



እግዚሐብሄር ኢትዮጵያና ህዝቦቾን ይባርክ!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!


ቃልኪዳን ካሳሁን (ከኖርዌ)

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar