søndag 27. mars 2016

ከብሄር በፊት ሀገር!!!

ከብሄር በፊት ሀገር!!!

በሀገራችና በህዝባችን ህወሓት ከሚፈፅማቸው ግፍና በደል በተጨማሪ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ሁኔታ የብሄርተኝነትን መርዝ አሰራጭቶል እያሰራጨም ይገኛል። ይህንም ያደረገበት ዋነኛ ምክንያት የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ሆን ብሎ ያደረገው ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱ የሆነ ብሄር እንዳለሁ ሁሉ ሰው ብሄርተኝነቱን እራሱ ፈልጎት የመጣ ነገር አይደለም፤ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው። ስለዚህ ህወሓት አሁን ላይ ስልጣኑን ለማራዘም ብሎ ብሄርን ከብሄር ማናከስ ትልቁ ስራው አድርጎታል፤ እያናከሰም ይገኛል። እስከመቼ በብሄር ፖለቲካ እያጫወተን እንዘልቀዋልን። ህወሓት ገና ጫካ እያለ አላማ አድርጎ የተነሳው የህዝቦችን አንድነት የመበጣጠስ አላማ አድርጎ የተነሳ ቡድን ነው።

አሁን ላይ በሀገራችን ያለው ስልጣን የአንድ ብሄር ስልጣን ነው። ይህ የአንድ ብሄር ስልጣን ለ25 አመታት በኢትዮጵያና በህዝቦቾ ታሪክ ግፍና በደል እንዲፈፀም አድርጓል። ህወሓት ብሄር ተደራጅቶ በሀገርና በህዝብ ላይ ይህ ነው የማይባል ኢፍትሃዊ ግፍና በደል ፈፅሟል፤ እየፈፀመም ይገኛል። መቼም አሁን አሁን እየተፈፀመ ያለው ግፍና በደል በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ይህም የሆነበት ምክንያት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በዜጎች ላይ የተወሰደው እኩይ ተግባር ይህ ነው የሚባል አይደለም።

የአንድ ብሄር ስልጣን ላይ መቀመጥ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ግፍና በደሎች ሰሚ አካል የላቸውም። ምክንያቱም ሀገሪቱና ህዝቦቾን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር አድርገውታል። ህግ አውጪ እነሱ፣ ህግ ተርጓሚ እነሱ፣ ህግ አስፈፃሚ እነሱ ይህ ሁኔታ ባለበት ሀገር ላይ የዜጎች የመኖር ዋስትና አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛሉ። ይህን የፈጠረው የአንድ ብሄር ስልጣን ስለሆነ በህዝባቸው የሚፈፀምባቸውን በደል ወይም ግፍ ለመቃወም የብሄር ትግል እንዲያስቡ ያስገድዳቸዋል። ነገር ግን የብሄር ትግሉ መደረጉ ባይጠላም፤ ሀገራዊ ትግል እንዲሆን መፈጠሩ ሁሉምንም ብሄር ያካተተ ያደርገዋል።

ህወሓት ሲታገል የነበርው አንድን ብሄር ነፃ ለማውጣት ታግሎ፤ አንድን ብሄር ለስልጣን አብቅቷል። ይህ ስርዓት አብዛኛውን ብሄር ብሄረሰብ  ጎድቶታል እየጎዳውም ነው። አንዳንቺን ለአንዳንቺን እንዳንያያዝ፣ እንዳንግባባ፣ እንዳንሰማማ፣ እንዳንተማመን…………….. ያደረገ ስርዓት ነው። የአንድ ብሄር ስልጣን የፈጠርውን ችግር እያየን የብሄር ትግል ውስጥ የገባን ልብ ብለን ልንገነዘብ ይገባናል። "አንድ ተረት አለ እሳትን ያየ በአመድ አይስቅም!!"

ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ሀገር ናት። እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ የራሱ የሆን ቋንቋና ባህል ወግ አለው። ለዘመናት ተከባብሮና ተፋቅሮ የኖረ ማህበረሰብ ነው። አሁን አሁን ህወሓት በፈጠረው ስርዓት ብሄር ከብሄር ጋር ሲያስማማ ወይም ሲያከባብር አልተስተዋለም። ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት በሀገሪቱ የአንድ ብሄር ስልጣን ዘመን እንዲራዘም ሆን ተብሎ የሚደረግ ድርጊት ነው።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዚህ ሶሻል ሚዲያ ላይ የሚስተዋሉ ነገሮች አሉ። እነዚሁ ነገሮች ብሄር እና ሀገር እየታገልን ያለነው ስለብሄር ነው ወይስ ስለሀገር የሚለውን ነገር እንድመለከት አድርጎኛል። ሁላችንም የእኔ የምንለው ብሄር አለን። እንዱሁም ሁላችንም በአንድ ስም ሊያስጠራን የሚችል ሀገርም አለን!! ታዲያ ትግላችን ከሀገር ወደ ብሄር እየሄደ ይመስላል።  አንድ ብሄር ብቻውን ህወሓት ተቃውሞ ከስልጣን ያስወግዳል የሚል እምነት የለኝም። ባይሆን ሁሉም በተቃውሞ ቢሳተፍ አንድ ደረጃ ላይ እንደርስ ነበር። እርግጥ ነው በብሄራችን ላይ የሚፈፀሙ ግፍና በደሎች ስለብሄራችን እንድንቆም ያደርጉናል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ተቃውሞ የለኝም። ነገር ግን እየሆነ ያለው ሁሉም   ስለእራሱ ብሄሩ የሚታገል ከሆነ ስለሀገራዊ ትግል እንዴት ልናስብ እንችላለን። እዚህ ጋር ቆም ብለን እናስብ!!  

ከብሄር በፊት ሀገር!! ሀገር እየፈረሰ ብሄር ይኖራል ማለት ዘበት ነው!! ይህ ደግሞ ማንም ሰው ሊያውቀውና ሊገነዘበው ግድ ይላል። ሀገርን ውስጥ ብዙ ህዝቦች አሉ!! አሁን ላይ ህወሓት ሀገርና ህዝብ እያጠፋ የሚገኝበት ሰዓት ላይ ነን ፤ይህ ደግሞ ከማንም የተደበቀ አይደለም። እርግጥ ነው ህወሓትና ቤተሰቦቻቸው ይህን እውነታ አይቀበሉትም። ምክንያቱ አላማ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ያሉት በሀገሪቱ ህዝብ ንብረትና ሀብት ላይ ስለሆን በህወሓት ላይ ምንም አይነት ተቃውሞ መስማትም ሆን ማየት አይፈልጉም።

ስለሆነም የምናደርገው ትግል ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች  ያማከለ መሆን አለበት ለጋምቤላው ህዝብ ኦሮሞው ካልጮህለት፣ ለኮንሶ ህዝብ አማራው ካልጮህለት፣ ለሀረሪ ህዝብ ትግሬው ካልጮህለት. . . . . . . . ጩህታችን ለመላው ለህዝባችን ካላደረግነው ተመልሶ እንደ ህወሓት አይነት ስርዓት መገንባቱ የማይቀር ነው።  ህወሓት ግፍና በደል መላው ህዝባችን ላይ ነው። ድምፅ ለሌላቸው ህዝቦች ድምፅ መሆን ካልቻልን አሁንም ይህ ፋሺስት ስርዓት በሀገሪቱና በህዝቡ ላይ የሚያደረሰውን መከራ ይቀጥላል። ይህ እንዳይሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከብሄር በፊት ለሀገሩና ለመላው ህዝብ  መቆም አለበት!! ሀገር ሲኖር ብሄር ይኖራል። አንድ ብሄር ሀገር መሆን አይችልም!! ሀገር ግን የብዙ ብሄር ብሄረሰብ ናት!!



እግዚሐብሄር ኢትዮጵያና ህዝቦቾን ይባርክ!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!


ቃልኪዳን ካሳሁን (ከኖርዌ)

tirsdag 22. mars 2016

የህወሓት አገዛዝ መቃወም ሀገር መጥላት አይደለም!!

                               የህወሓት አገዛዝ መቃወም ሀገር መጥላት አይደለም!!

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ያደረኩት ነገር ቢኖር በስርዓቱ ደጋፊዎች ዘንድ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። ከሚሰነዝሯቸው ሀሳቦች በተደጋጋሚ የምመለከትው ነገር ቢኖሮ የህወሓት አገዛዙ መቃወም ማለት ሀገር መጥላት አድርገው ሲገነዘቡ አስተውያለው።

በመጀመሪያ ደረጃ ህወሓትና ሀገር ይለያሉ!! ህወሓት ማለት የአንድ ብሄር ስብስብ ሲሆን፤ በትጥቅ ትግል ታግሎ ስልጣን የያዘ አንድ ቡድን ነው። ሀገር ማለት ብዙ ህዝቦችን፣ ብዙ ቋንቋዎችን፣ ብዙ ብሄሮችን፣ ብዙ ጎሳዎችን፣ ብዙ ባህሎችን፣ ብዙ እሴት. . . . . . . . . . ይዛ የምትኖር ማለት ነው። ከልዩነታቸው ተነስተን ብዙ ነገር ልንገነዘብ እንችላለን። እርግጥ ነው ይህ ሊናገሩ የሚችሉት ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ነው። አንድ አባባል አለ “አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል” አይደል የሚባለው። ህወሓት ተቃውሞ ሲገጥመው ጥቅማቸው የሚነካባቸው አካላት አሉ፤ ለዚህም ነው ስርዓቱን ለሚቃወሙ ሰዎች ሀገራቸውን እንደሚጠሉ ተደርጎ የሚታዩት።

የህወሓት አገዛዙን መቃወም ሀገር መጥላት ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የለም። ህወሓት በሀገሪቱና በህዝቦቾ ላይ የሚፈፅመውን እኩይ ተግባር መቃወም ከሀገር መጥላት ጋር ሊያገናኙ የማይችሉ ነገሮች ናቸው። ህወሓት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን ድረስ በዜጎች ላይ የሚደረሰው ስቃይና መከራ ቀጥሏል። በመከራና ስቃይ ውስጥ ሆነው ሲቃወሙ እጣ ፈንታቸው ሞት ወይ እስራት በሆነበት ስርዓት ውስጥ ህወሓትም ሆን ደጋፊዎች ስርዓቱን መቃወም ሀገር እንደመጥላት ይመለከቱታል።

ሀገር መጥላት ለሚባለው ነገር፤ ማንኛውም ሰው ስለሀገሩ ልዩ ፍቅርና ክብር አለው። ስለሀገሩ ክብርና ፍቅርም ብዙ መሰዋዓትነት የሚከፍል፤ እየከፈለም የኖረ ህዝብ ነው። በየትኛውም አለም ላይ ሀገሩን የሚጠላ ህብረተሰብ የለም። በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ስርዓት መወደድም ሆን መጠላትም በመንግስትና በህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ይወስነዋል።  ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ እንደ መንግስት ሆኖ ሀገሪቱን እየገዛት ያለው የአንድ አካባቢ ተዋላጆች ብቻ በመሆኑ በህዝቦች እና በገዥው ስርዓት መካከል በጣም ከፍትኛ ችግር ይገኛል።

አሁን ላይ ህወሓትን መቃወም ማለት ከህዝብና ከሀገር ጎን መቆም ማለት ነው። በዚህ ወቅት በመላው ሀገሪቱ የአገዛዝ ስርዓቱን በመቃወም ላይ ይገኛሉ። ይህ ተቃውሞ ስርዓቱ በፈጠረው ተፅዕኖ የመጣ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተቃውሞ ይበልጥ መጠናከሩ ሁኔታ በሀገሪቱ ላይ የመሬትን ወረራን በተመለከት ተቃውሞውን ይበልጥ አጎልቶታል። ህወሓትና ቤተሰቦቻቸው በአሁን ጊዜ በሀገሪቱ ላይ ከፈተኛ የመሬት ወረራ ላይ መጠመዳቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተገነዘበው ጉዳይ ነው።

ስለ ህወሓት ተቃውሞ በተመለከት ገና ከጅምሩ ሲታገል የነበረው አንድን ብሄር ነፃ ለማውጣትና የሀገሪቱን ታሪኳን ለማጥፋት ሲታገል የመጣ ቡድን ነው። ይህው በ25 አመታት ውስጥ በኢትዮጵያዊን ዜጎች በውጭም ሆን በሀገር ውስጥ የሚደርሱ አሰቃቂ ግፎች የዚህ ስርዓት ቅጥ ያጣ ስልጣን መከት ያደረገ መሆኑ ነው። እነዚህና ሌሎች ችግሮ በመመልከት ነው ተቃውሞ ከዕለት ወደ ዕለት ሊበረታ የቻለው።

ይህ ህዝብ ለስርዓቱን አልገዛም ማለቱ ሀገሩን እንደሚጠላ መታሰቡ የሚገርም ነው!! በህወሓት ዘመን ዳር ድንበር የተደፈረበት፣ ዜጎች የሚገደሉበት፣ የሚታሰሩበት፣ የሚሰደዱበት፣ የሚፈናቀሉበት ዘመን. . . . . . . ከዚህ ዘመን የተረፈን መከራና ውርደት ነው። ይህን መቃወም ሀገር መጥላት ሊባል አይገባም፤ ለሀገር ተቆርቋሪነት እንጂ እንሱ ይህን እኩይ ተግባር በሀገሪቱና በህዝቡ ላይ እየፈፀሙ ሀገር ጠሉ አልተባሉም።

ይህን አስመልክቶ ለሚነሱ ተቃውሞው በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ ስም በካድሬዎችም ሆን በደጋፊዎቻቸው ሲሰጡ ይስተዋላል። ምንም አይነት ስም ቢሰጥም ህወሓትን ከመቃወም የሚሰንፍ የለም።


እግዚሐብሄር ኢትዮጵያና ህዝቦቾን ይባርክ!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
ቃልኪዳን ካሳሁን (ከኖርዌ)

søndag 20. mars 2016

ህወሓትና የእምነት ተቋማት!!

ህወሓትና የእምነት ተቋማት!!

ከሌሎች ሀገራት እኛ ኢትዮጵያዊያን ለየት ከሚያደርጉን ነገሮች መካከል የሀይማኖት መቻቻል ነው።  በሀገራችን በኦርቶዶክስና በእስልምና ሃይማኖቶች መካከል ያለውን ለረዥም አመታት ተከባብሮና ተቻችለው የሚኖሩ  ሃይማኖቶች ናቸው። እነዚህ ሁለት የእምነት ተቋማት በእለት ተዕለት የአምልኮ ስርዓታቸው ዘወትር የሚከናውነው በራሳቸው የእምነት ስነ ስርዓት ነው። ይህ ደግሞ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአምልኮ ስርዓት መሆኑ በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ ነው።

አሁን አሁን በሀገራችን ውስጥ እየታየው ያለው ነገር ለማመን በሚቸግር መልኩ ነው። ይህን ያልኩበት ዋነኛ ምክንያት አንዳንድ የህወሓት ካድሬዎች በእምነት ተቋማት ውስጥ እየተዘወተሩ መተዋል። በተለይ በኦርቶዶክስ እምነት ተቋም ውስጥ መዘውተሩ እየተለመደ መቷል። ይህ አካሄድ በእጁጉ ልንቃወመው የሚገባ ነገር ነው። ቤተ እምነት ማለት እግዚሃብሄር የሚመለክበት እንደመሆኑ መጠን የመንግስት ስራ ማስፈፀሚያ ሲሆን ዝም ብሎ ማየቱ ተገቢ አይደለም።

ህወሓት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሁለቱም በእምነት ተቋማት ውስጥ እየፈጠረ ያለውን ችግሮች ቀላል የሚባሉ አይደሉም። በሙስሊም እምነት ተከታዮች ላይ እየፈፀመ ያለው ግፍ ዝም ሊባል የሚገባ አይደለም። ስለሀይማኖታቸው ለሚቆሙ ሰዎች “አክራሪ” ወይም “አሸባሪ” የሚባል ስም ይሰጣቸዋል፤ ብሎም ለእስራት ይዳረጋሉ። ይህ ነገር እስከመቼ? በእንዲህ አይነቱ ይዘለቃል። ሌላኛው ደግሞ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚስተዋሉ ችግሮች እየበዙ መተዋል፤ ለዚህም እንደማሳያ የምንመለከተው በማህበረ ቅዱሳን ላይ አዲስ ዘመቻ በመክፈት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የማስጠላት ስራ እየሰሩ መሆኑን ከማንም የተደበቀ አይደለም።

ይህ ሁኔታ በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ በሁለቱም የእምነት ተቋማት ውስጥ አሁን ከምናየውና ከምንሰማው ይበልጥ ችግሩ የከፋ ይሆናል። “ህወሓት በአሁን ሰዓት እጁ በጣም እረዝሟል።” በሁለቱ እምነት ተቋማት ላይ ካነጣጠር ጊዜያው ገፍቶል።

እያንዳንዳችን በየእምነታችን ተቋማት ውስጥ የተሰገሰጉትን የህወሓት ካድሬዎች ልንቃወም ይገባል። የእምነት ተቋማት ለህብረተሰቡ የአምልኮ አገልግሎት መስጫ እንጂ የመንግስት ፕሮፖጋንዳ ማስፈፀሚያ መሆን የለባቸውም። ህወሓት አሁን ላይ ታጥቆ የተነሳበት አላማ በየእምነት ተቋማቱ የራሱ የሆኑ ካድሬዎችን መልምሎ ለማስቀመጥ በሰፊው እየሰራበት ይገኛል። ስለዚህ ወገኖቼ የህወሓት መጠቀሚያ ከመሆን እንቆጠብ።
“ለየሀይማኖታችን ዘብ እንቁም!!”
እግዚሐብሄር ኢትዮጵያና ህዝቦቾን ይባርክ!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!



ቃልኪዳን ካሳሁን (ከኖርዌ)

lørdag 19. mars 2016

የፖለቲከኞችና የህሊና እስረኞች የአቋም ፅናት!!


የፖለቲከኞችና የህሊና እስረኞች የአቋም ፅናት!!

ህወሓት በስልጣን ዘመኑ በህዝቡ ላይ ብዙ እየፈፀማቸው ያለው ግፍ በዝቶል። በተለይ ከጥቂት አመታት ወዲህ የፀረ ሽብር ህጉን በማስታከክ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚያደርሰው ግፍ ይህ ነው ተብሎ የሚነገር አይደለም።

ህወሓት ይህን የፀረ ሽብር አዋጅ ያረቀቀበት ዋንኛ ምክንያት የዜጎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች ሽብርተኛ ናቹ በማለት ለአገዛዙ እንዲመቸው አድርጎ ቀርፆታል። ይህ የሆነበት ዋንኛ ምክንያት የህወሓት አገዛዙን ለሚቃወሙ እንደማፈኛ ወይም እንደማስፈራሪያ የሚጠቀመው ህግ ነው።

ለዚህም ዜጎች ለዚህ አዋጅ ሰለባ የሆኑ እንዳሉ ሁላችንም የምናውቀው ነው። የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በዝተዋል። ለዚህም ዋንኛ ምክንያት አድርገው ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ተንቀሳቀሳቹሃል በማለት  ዜጎች ላይ ከ5 አመት እስክ እድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ፍርደኞች ይገኛሉ። እነዚህ ፍርደኞች ያለምንም ማስረጃ በየማጎሪያ ቤቱ ይማቅቃሉ፣ ይሰቃያሉ ብሎም ለሞት ይዳረጋሉ። የእስራት ጊዜአቸውን ጨርሰው የውጡም ጥቂት ግለሰቦችም በእስር ቤቱ ይደርስባቸው የነበርውን እንግልት በጣም ዝግናኝ እንደሆን ሁላችንም እየሰማንና እያየን እንገኛለን።

እኔ አንድ የተደነኩበት ወይም ያስገረምኝ ነገር ቢኖር በእስር ላይ የሚገኙትም ሆን ከእስር የተለቀቁት እስረኞች አንድ አይነት አቋም አላቸው። በህወሓት እጅ ላይ ወድቆ እንዲህ ያለ የአላማ ፅናት በእጅጉ የሚያስደምም ነው። ይህ የአቋም ፅናት የመጣው እንዲሁ በከንቱ አይደለም፣ ዋጋ ተከፍሎበታል፣ እውነትን ይዘዋል፣ ስለህዝባቸው፣ ለሀገራቸው በእውነት ፀንተዋል። በህወሓት የሚደርስባቸውን ስቃይና መከራ ተቋቁመው በዛ መራር እስር ቤት ሆነው ለህዝቡ የሚሰጡት ተስፋ ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋ አለው።

በመከራና ስቃይ ውስጥ ሆነ ስለህዝብ፣ ስለሀገር፣ ስለፍትህ፣ ስለመብት፣ ስለዲሞክራሲ ማሰቡ እጅግ የሚያስደንቅ ተግባር ነው። መቼም በዚህ ዘመን እንዲህ አይነቱን የአላማ ፅናት ለህወሓት እጅግ ከባድ ራስ ምታት ነው። እነዚህ ለነፃነት እና ለመብት መከበር ለሚታገሉ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ዘወትር ሊወደሱ ይገባቸዋል። እንደማናችንም ሰው ናቸው፤ ቤተሰብ አላቸው ናቸው!! እነሱ ከእኛ የሚለያቸው ስለሀገርና ስለህዝብ ዘወትር ፀንተው በተግባር ያሳዩ መሆናቸው ነው።

የፀረ ሽብር አዋጁ እስካለ ድረስ ዜጎች በሚያደርጉት እለት ተዕለት እንቅስቃሴ አደጋ ውስጥ ነው። ይህ እንዲህ ባለበት ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በተጠናከረ መልኩ እንደቀጠለ ነው። ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ለሁለት አስር አመታት የስርዓቱ የፈጠረው ትልቅ ተፅዕኖ መሆኖ ነው።


ሁላችንም በአቋማች እንፅና!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

ቃልኪዳን ካሳሁን (ከኖርዌ)

fredag 11. mars 2016

ሴት መሆን ምንም ከማድረግ የሚከለክል ነገር የለም!!

ሴት መሆን ምንም ከማድረግ የሚከለክል ነገር የለም!!

እነዚህን እንስቶች መቼ በፌስቡክ መንደር ማየት ከጀመርን ሰንበት ብለናል። ስለነዚህ እንስቶችን ብዙ ማለት አልችልም። ምንም የማለት የሞራል አቅመም የለኝ። እንስቶች ለሀገራቸው እየከፈሉት ያለውን መሰዋትነት ቀላል የሚባል አይደለም።
እነሱ እንደ እኛ ሰው ናቸው። ያውም ሴት ወጣትነት የሚታይባቸው ሴቶች!! ሴትነት ሳይበግራቸው ከትግል ጎራ መቆማቸው በዚህ ዘመን ልዩና ልዩ ያደርጋቸዋል። እርግጠኛ ነኝ አጋንንሺው እንደማትሉኝ።
ሴት መሆን ምንም ከማድረግ የሚከለክል ነገር የለም። በተግባርም አሳይተዋል!! ደግሞሞ በ21 ክፍለ ዘመን ላይ ሆነው ያሳዩን ሴቶች ናቸው። በዚህ ዘመን ላይ እንዲህ ያሉ ሴቶችን ማግኝቱ እጅግ የሚደነቅ ነው።
እነዚህ እንስቶች እንደሰው ሁሉ ነገር የሚያምራቸው ናቸው። ማግባት፣ መውለድ፣ መማር፣ በቃ በዘመኑ ሴቶች የሚያደርጉትን ነገሮቹ ሁሉ ቢያደርጉ የማይጠሉ። ነገር ግን እነሱ ይህ የምንላቸውን ነገር በመተው ነው ትግል ጎራ መገኘታቸው ልናደንቃቸው ግንድ ይለናል።
የእነዚህ እንስቶች ፎቶዎች ባየዋቸው ቁጥር ብዙ ነገር ይሰማኛል። ይህን ስል በውስጣቸው ያለው ተስፋ አለመቁረጥ፣ የሀገር ፍቅር፣ የህዝብ ፍቅር፣ የሰንደቅአላማ ፍቅር......ኧረ ስንቱን!!
ክብር ለእነዚህ እንስቶች!!
ቃልኪዳን ካሳሁን

torsdag 10. mars 2016

በእኛ ዝምታ እነሱ ጀገኑ!!

በእኛ ዝምታ እነሱ ጀገኑ!!

ምን ብዬት መጀመር ግራ አገባኝ....... የቱን አንስቼ የቱን ልተው...... ምንስ ብፅፍ የውስጤን ቁጭት ይገልፀዋል......!! በህዝባችን ላይ እለት ተዕለት  እየተፈፀመ ያለውን ግፍና ሰቆቃ እየሰማንና እያየን እስከመቼ.....በዝምታ እንኖራለን ግፉ ፅዋ ሞልቶ ፈሷል። ዜጎች በራሳቸው ሀገር፣ በራሳቸው መንደር፣ በራሳቸው ማንነት እንዳይኖሩ የሚደረግበት ሀገር ኢትዮጵያ!! 

ትናንት በኦሮሞና በጋምቤላው ወገናችን ላየ በደረሰው ኢሰብዓዊ ድርጊት ምን ያህልን ውስጣችን ስንቃጠል እንደከረምን ከሁላችን የማንረሳው ነው። ይባስ ዛሬ ደግሞ የገደሉትን ገለው፣ያሰሩትን አስረው ፣ይህ አለበቃ ሲላቸው የሰው ልጅ ከሰው ጋር አስሮ ማሰቃየት ላይ ደርሰዋል። ይህን እኩይ ተግባር ማየቱንም ሆን መስማቱ እንዴት እንዴት ያማል.....!! "በእኛ ዝምታ እነሱ ጀገኑ!!"

ስማኝ ልንገርህ ወገኔ ዛሬ ሱርማ ወገናች ላይ የተፈፀመው እኩይ ተግባር ነገ በእኔና በአንተ የገዛ ቤታችን ውስጥ መተው እንደሚያድርጉት አትጠራጠር። 21 ክፍለ ዘመን ላይ እየኖረን ኑሮቻች እና ስቃያችን 18 ክፍለ ዘመን ሆኖል። ይህን ግፍና ሰቆቆ እስከመቼ በዝምታ እንደምንገልፀው!!  

ጥቂቶች መብታቸውን ተከብሮ ነገር ግን ብዙሃኑ መብቱን እና ነፃነቱን ተነፍጎ የሚኖርባት ሀገር ኢትዮጵያ እየሆን ያለው በህዝባችን ላይ በእውነቱ ዝም የሚያስብል አይደለም። አሁን አሁንማ መብት ሲጠየቅ ምላሹ በመሳሪያ ሆኖል።  "በእኛ ዝምታ እነሱ ጀገኑ!!"

ይህን ግፍና መከራ እየሰማን፣ እየተመለከትን ስለምን ዝም አልን፣ ስለምን ዝምታን መረጥን፣ ስለምን በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን ስቃይና መከራ ለማውገዝ አቅም አጣን፣ ስለምን የወገናችንን ሞት ሞታችን ማድረግ አቃተን፣ ስለምን መንገድ ዳር ስለሚገድሉብን ልጆች፣ እናቶች፣ ወጣቶች እንዲሁም አዛውንቶች እየሰማንና እያየን ዝምታን መረጥን!!

የእኛን ዝምታ እነሱን ካጀገነ ችግሩ እነሱ ጋር ሳይሆን እኛው ጋር ነው። ስለዚህ ስማኝ ልንገርህ ወገኔ ህወትን ከስልጣን ለማወረድ የእኛ ዝምታችን ሰባብረን በአንድነት ስንጮህ ነው። ተደራጅ፣ ተሰባሰብ፣ ተወያይ..........."የሀገር ጉዳይ ነውና" እንክፈል ጊዜችን፣ እንክፈል ገንዘባችን፣ እንክፈል ህይወታችን.........ነፃነት ዋጋ ታስከፍላለችና ያለ መሰዋትነት ድል የለምና መከፈል ላለበት መክፈል አለበት......... "ኢትዮጵያ ደምና አጥንት የተከፈለባት ሀገር ናት" አሁንም ልንከፍል ግድ ነው!! "በእኛ ዝምታ እነሱ ጀገኑ!!" 

በህዝቡ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እንቢተኝነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በህዝባዊ እንቢተኝነቱን እንዲሳተፍ የየበኩላችን ጥረት እናድርግ ኢትዮጵያና ህዝቦቾን ከዚህ ፋሽስት ስርዓት እንታደግ!!

"ህወሓት እስካለ ተቃውሞ አለ"

ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!!
ድል ለጭቁኑ ህዝብ!!

ቃልኪዳን ካሳሁን   (ከኖርዌ)