mandag 3. februar 2014

የአማራውን ሕዝብ ክብር የደፈሩና ያዋረዱ አምባገነን ገዥዎች ለፍርድ ይቅረቡ!!!


ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
=================================
‹‹ጉድ ሳይሰማ…›› እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በስርዓቱ እየተፈፀመበት ካለው ጭቆናና በደል፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ገፈፋ፤ አፈናና ስደት፤ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት በተጨማሪም በአምባገነን ገዥዎች እየተዋረደ፣ በአደባባይ እየተሰደበና ሰብዓዊ ክብሩ እየተጣሰ ይገኛል፡፡ 

እንዳለመታደል ሆኖም ሀገራችን ላይ ያለው ስርዓት ህዝቡን የሚያዋርድ፣ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ስልጣኑን የሚያስቀድም፣ ለህዝብ ጆሮ የሚሰጥ አስተዋይ መሪ የሌለው ነው፡፡ ለዘመናት ያልተፈቱ ችግሮችና በመሪዎቹ የሚፈጠሩ ችግሮች ትከሻውን ያጎበጡት የኢትዮጵያ ህዝብም ስርዓቱን ከነችግሩ መሸከሙ አልበቃ ብሎ መሪ ነን በሚሉት እየተበሻቀጠና ለውርደት እየተዳረገ ይገኛል፡፡

ፓርቲያችን በትኩረት እየተከታተለው ያለውና ሰሞኑን የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይና በኢሳት ይፋ የተደረገው የአማራ ክልል ም/ ፕሬዘዳንትና የብአዴን ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን የአማራውን ህዝብ በአደባባይ መሳደባቸውንና ማዋረዳቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች መለቀቃቸውና የክልሉ መንግስት ለማስተባበል እንኳ ዝግጁ አለመሆኑ የሚያሳየው ንቀትንና ጥላቻን ብቻ ሳይሆን እንመራዋለን የሚሉት ህዝብ ትከሻ ላይ ተቀምጠው ፀረ ህዝብ አቋም እንደሚያራምዱ ነው፡፡ ፓርቲያችን የብአዴን/ኢህአዴግ ባለስልጣን በአማራ ህዝብ ላይ የፈፀሙትን ክብር የሚነካ አሳፋሪ ድርጊት በቸልታ ሊመለከተው እንደማይችል አስረግጦ ለመናገር ይወዳል፡፡ ፀረ ህዝብ አቋም የሚያራምዱ አምባገነኖችንም ከህዝብ ትክሻ ለማውረድ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡ አንድነት በቅርቡ በጉራ ፈርዳና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በዜጎች ላይ የተወሰደው የማፈናቀል ተግባር ስርዓቱና የስርዓቱ መሪዎች የፈጠሩት ችግር እንጅ የአካባቢው ሕዝብ የፈጠረው እንዳልሆነ ያምናል፡፡

አቶ አለምነው መኮንን የተባሉት ባለስልጣን የአለቆቻቸውን የዘወትር አባባል በማስረገጥ እመራዋለሁ የሚሉትን የአማራ ህዝብ ‹‹ሰንፋጭ የሆነ ትምክህተኝነት የተጠናወተው፣ ትምክህተኝነቱን ያልተወ፣ በባዶ እግሩ እየሄደ መርዝ ንግግር የሚናገር ወዘተ›› ካሉ በኋላ ‹‹የትምክህት ልጋጉን ማራገፍ አለበት›› በማለት እንደሌሎች ብሄረሰቦች ሁሉ ለዚች ሀገር ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል ዋጋ የከፈለውን የአማራ ህዝብ ዋጋ በማሳጣትና የሌሎች ጠላት አድርጎ በማቅረብ የማጥላላት ዘመቻ ከፍተዋል፡፡
ፓርቲያችንም ይህንን አሳፋሪና የዜጎችን ክብር የደፈረ የባለስልጣኑ አባባል በቸልታ የሚታይ ሆኖ አላገኘውም፡፡
ስለዚህ፡-
1. ግለሰቡ በዚህ የተዛባ አመለካከቱ ለአማራ ህዝብ መሪ ሊሆን ስለማይችል በአስቸኳይ ከፓርቲና ከመንግስት ኃላፊነቱ እንዲነሳና ለህዝቡ ይፋ እንዲደረግ፤
2. ህዝቡን ያዋረደው ባለስልጣን ላይ ርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ግን የግለሰቡ አመለካከት የብአዴንና የክልሉ መንግስት አቋም አድርገን የምንወስድ መሆኑ እንዲታወቅ፤
3. አንድነት ፓርቲ ፀረ-ህዝብ አቋም ያለው ግለሰብ ባደረገው የህዝብ ጥላቻ ንግግር (Hate speech) ተነስቶ ለሕግ የሚያቀርብ መሆኑ እንዲታወቅ፤
4. ፓርቲያችን ህዝቡን በማስተባበር በባህርዳር ከተማ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚጠራና ድርጊቱን የማውገዝና እንዲቆም የማድረግ ርምጃ የሚወስድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
ስለዚህ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የክልሉን ህዝብ እየመራው ያለው ብአዴን/ኢህአዴግ ለህዝብ ክብር የሌለው ድርጅት መሆኑን አውቆ ከፓቲያችን ጎን በመቆም እንዲታገለው ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

søndag 2. februar 2014

ሰማያዊ ፓርቲ በብዙ አፈና ታጅቦ በጎንደር የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ አከናወነ


“ተከብሮ በኖረው በአባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ ያስደፈረሽ ይውደም”
ዛሬ በጎንደር ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሕዝብ በአንድ ላይ የሃገሩን ድንበር ተቆርሶ ለሱዳን መሰጠቱን ለመቃወም የዘፈነው ዘፈን ነው። ገና ከቅስቀሳው ጀምሮ በስርዓቱ ፖሊሶችና የደህነት ሰራተኞች የዛሬው ሰልፍ እንዳይሳካ ከፍተኛ የሆነ መሰናክል ቢገጥመውም በጎንደር የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በሰላም ሲጠናቀቅ፤ አንዳንድ የሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊዎች እና አባላት አሁንም ከሰልፉ በኋላ መታሰራቸው አልቀረም።
በሰልፉ ቅስቀሳ ወቅት የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ የጎንደር አባላት እና ደጋፊዎች “ሕገ ወጥ ስልፍ ነውና አትቀስቅሱ” በሚል ታስረው የተፈቱ ቢሆንም “ሕገ መንግስታዊ መብታችን መንግስትን ሰላማዊ ሰልፍ እንደምናደርግ ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ የለብንም” በሚል እስከ መጨረሻው ድረስ ባደረጉት ትንቅንቅ እየታሰሩ መፈታት፣ መንገላታት ቢደርስባቸውም ሰልፉ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተደርጓል።
gonder-2-blue
በጎንደር መስቀል አደባባይ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች ወጥተው ለሱዳን የተሰጠውን እና የሚሰጠውን መሬት ጉዳይ የተቃወሙ ሲሆን መንግስት የሃገርን ዳር ድንበር ከመሸጥ ተግባር እንዲቆጠብ ጠይቀዋል። መሬት ከመስጠት እንዲቆጠብ ከመጠይቅም በላይ መንግስት በአሁኑ ወቅት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ መረጃ እየሰጠ ባለመሆኑ፤ በተቃራኒው የሱዳን መንግስት ስለተበረከተለት መሬት በሚዲያዎቹ በሰፊው እየለፈፈ በመሆኑ፤ ለሕዝቡ መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት ሲሉ የተቃውሞ ሰልኞቹ መጠየቃቸውን ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
ለዘ-ሐበሻ እንደደረሰው መረጃ ከሆነ የጎንደር ከተማ ትራፊክ ፖሊስ ከበላይ በመጣ ቀጭን ትዕዛዝ በዚህ ታሪካዊ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ለመታደም ወደዚያው የሚተመውን የጎንደር ሕዝብ የትራፊክ መንገድ በመዝጋት ወደ መስቀል አደባባይ እንዳይሄድ ሲያከላክል እንደነበር ተገልጿል። 5ለ1 የተደራጁ የሥርዓቱ ደጋፊዎች ወደ ሰልፍ ለመሄድ የሚዘጋጁትን እና እየሄዱ ያሉትን ለማሸማቀቅ ቢሞክሩም ሕዝቡ ወጥቶ ድምጹን ከማሰማት እንዳላገደው መረጃው ያመለክታል። እነዚሁ ኢህአዴግ 5ለ1 ያደራጃቸው ግለሰቦች (ጠርናፊና ተጠርናፊዎች) ሰልፉ ተሰርዟል በሚል በጎንደር ሰፊ ቅስቀሳ ባማድረግ ነጻ ሚድያ የማይሰማውን ሕዝብን ሲያሳስቱ እንደነበር ተገልጿል።
ዛሬ በጎንደር የተደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ ያስተባበሩት ለህብረተሰቡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ባሰሙት ንግግር “በዚህ አስቸጋሪ ወቅትና አምባገንን ስርዓት ውስጥ ሆናችሁ፤ የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ብላችሁ ስለመጣችሁ እናመሰግናለን” ካሉ በኋላ ሰላማዊ ሰልፉ ታዳሚ ይህ ሰልፍ ለምን ሊደረግ እንደቻለ አብራርተዋል። በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያም ገለጻ አድርገዋል።
በሰልፉ ላይ የተገኙት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው “ወጣቶች የሃገራችሁን ክብር ለማስጠበቅ ራሳችሁን ከፍርሃት አላቁ። ከፍርሃት እና ከሥጋት ወጥታችሁ ለሃገራችሁ አለኝታ ሁኑ” ብለዋል። ለሥርዓቱ መሪዎችም “ሥልጣን ወቅታዊ ነው፤ ያልፋል። በኢትዮጵያ ዳር ድንበር ላይ የሚጸመው ደባ ግን አያልፍም” ካሉ በኋላ ይህን ታሪካዊ ስህተት እንዲያስቆሙ በንግግራቸው ላይ እንደጠየቁ የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ከጎንደር ዘግበዋል።
“የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ለልጆቻቸው ጥሩ ታሪክን እንጂ ውርደትን ማውረስ የለባቸውም” በማለት የተናገሩት ኢንጂነር ይልቃል በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዛሬ ፌብሩዋሪ 2 ቀን 2014 በጎንደር በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ሕዝቡ
“ሉዓላዊነታችንን አናስደፍርም”
“ወያኔ አይወክለንም”
“እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም”
“አባቶቻችን ያስረከቡንን መሬት አሳልፈን አንሰጥም” የሚሉም የተቃውሞ መፈክሮችን ሲያሰማ ነበር።

ሌንጮ ለታ – ታሪክ ሊሰሩ ወይንስ ታሪክ ሊጽፉ…?


ኢትዮጵያዊው ቱጃር ለለውጥ ብለው በኮንትራት ታክሲ በመሄድ ላይ ናቸው። እሳቸውን የጫነው ታክሲ መስቀል አደባባይ ላይ ሲደርስ በድንገት ቀጥ ብሎ ቆመ። ሾፌሩ ተደናጋጠ። መኪናውን እንደገና ለማስንሳት ብዙ ሞከረ። ከብዙ ሙከራ በኋላ ጥረቱ ስላልተሳካለት ቱጃሩን ለትብብር ጠየቃቸው። እንዲህ ሲል። “ወጣ ብለው ይግፉ።” ቱጃሩ በመገረም ሾፌሩን አዩት። “ይግዙ” ማለትህ ነው ሲሉም መለሱለት። እኚህ ሰው መኪናውን ከመግፋት ይልቅ አዲስ መኪና መግዛት ይቀላቸዋል። የቤቶች ድራማ ላይ እከ ደከ አስር ጊዜ “እኔን ነው?” የሚለው ወዶ አይደለም። ማመን የሚቸግሩንን ነገሮች ማጣራት ስንፈልግ እንደጋግማለን።
በዚያን ሰሞን በኦቦ ሌንጮ ለታ የወጣው ዜና ብዙዎችን አስገርሟል።
odf-lencho-leta“ሃገር ቤት ገብተን በመታገል አዲስ ታሪክ እንሰራለን።” የሚል ነበር የዜና እወጃው ርዕስ። ይህን ርዕስ እንዳየሁ አይኔን በደንብ ጠረግ ጠረግ አደረግኩና እንደገና አነበብኩት።
“ታሪክ እንሰራለን” የሚለው ሃረግ በስህተት የሰፈረ ነበር የመሰለኝ። ሌንጮ ለማለት የፈለጉት “ታሪክ እናነባለን” ይሆናል በሚል ጥርጣሬ ደጋግሜ ያየሁት። ያነበብኩት ነገር ትክክል ነው። ይህንኑ ቃል ከራሳቸው አንደበትም ሠማሁ። በስህተት የሰፈረ ዜና አልነበረም። ታሪክን ማንበቡም ሆነ መስራቱ ቀርቶ “ሃገር ቤት ገብተን አዲስ ታሪክ እንጽፋለን።” የሚል ቢሆን እንኳን ግርታውን ይቀንሰው ነበር።
በፍትህ ሳይሆን ይልቁንም በአዋጅ በምትተዳደር ኢትዮጵያ፤ እጅና እግራቸውን ብቻ ይዘው በመግባት ታሪክ መስራት የሚችሉ ከሆነ በምትሃት አልያም በመለኮታዊ ሃይል ብቻ መሆን አለበት። ሌንጮ ሃገር ቤት ገብተው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰናቸው ላይ ምንም ችግር የለብኝም። የዚህ ውሳኔ ትክክለኝነት የሚዳኘው አስቀድመው በሚተቹ እና በሚተነብዩ የፖለቲካ ነብያት አይደለም። ፍርድ የሚሰጠው ሂደቱ በተግባር ሲፈተን ብቻ ይሆናል። ይህን ለማየት ደግሞ ብዙም ሩቅ አይሆንም። በጎረበጠ የፖለቲካ መንገድ ላይ ጉዞ ለማድረግ ወደ ሃገር ቤት ለመግባት መወሰናቸው ግን አስመራ ላይ፤ በሻእቢያ ከታገቱት የኦነግ መሪዎች የተሻለ ውሳኔ ይመስላል። ታሪክ ለመስራት አስመራ የመሸጉት እነ ዳውድ ኢብሳ ታሪክ ሆነው ቀርተዋል።
ችግሩ ያለው “ታሪክ እንሰራለን” ማለቱ ላይ ነው። እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ትግል ውሳኔ ላይ መድረስ ቀላል ነገር አይደለም። ከመቅጽበት የመጣው ይህ ውሳኔ ልክ እንደ ኦሎምፒክ ውድድር ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ አትሌት ይመስላል። አትሌቲክስም ቢሆን የአካል ብቃትና በቂ ዝግጅትን ይጠይቃል። ፖለቲካ ደግሞ ዘው ብለው ገብተው ታሪክ የሚሰሩበት በኦሎምፒክ የውድድር መድረክ አይደለም። እነ ሌንጮ እየነገሩን ያሉት አዲስ አበባ ገብተው በባላገሩ አይደል ላይ ለመወዳደር አይደለም። በባላገሩ የጫወታ ደንብ ጥሩ ስራ የሰራም፤ አስቀያሚ ስራ የሰራም ይሸለማል። ሌንጮ ታሪክ እንሰራለን የሚሉት “ስልጣን ወይንም ሞት!” የሚል መፈክር አንግቦ እስካፍንጫው የታጠቀ ሃይልን በመጋፈጥ ነው።
ታሪክን ለመስራት ብቃት ያላቸው ድርጅቶች በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ጠፍተው አያውቁም። ከኦሮሞ ድርጅቶችም ቢሆን እነ ኦቦ ቡልቻ ደመቅሳ እና ፕ/ር መረራ ጉዲና አሉ። የኦሮሞን ህዝብ አደራጅተው በምርጫም፣ በፓርላማም፣ በሰልፍም፣ በእርግማንም፣ በጸሎትና ምልጃም፣ በወረቀትም … ብዙ ተጉዘዋል። የእነዚህ ድርጅቶች አባላት እንደጥጃ እየተለቀሙ እስር ቤቱን ከማጨናነቃቸው በቀር ታሪክ ሲሰሩ አላየንም። አንድ እርምጃ ወደፊት፤ አስር እርምጃ ወደኋላ እየተጓዙ ሄደው…ሄደው በመጨረሻ ራሳቸውም ታሪክ ከመሆን አላለፉም። ይህ ለአቶ ሌንጮ ለታ እንግዳ ነገር አይደለም። አቶ ሌንጮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በከባድ ሚዛን ደረጃ የሚመደቡ ናቸው።
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በፖለቲካ ታግሎ ታሪክ ከመስራት ይልቅ ነድጅ ቆፍሮ ታሪክ መስራት እንደሚቀል ለሌንጮም አዲስ ነገር አይደለም። እርግጥ ነው። የታሪክ ትርጉም አሰጣጣችን ላይ እንለያይ ይሆናል። የገዥው ፓርቲ የታሪክ ትርጉምም ከልማት ጋር ይያያዛል። በዘመናችን ብዙ ታሪኮችን እየሰማን ነው። ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ሁሉ ዛሬ ታሪክ ሰሪ ይባላል። ታሪክ ሰርተው የሚሸለሙ የልማት አርበኞችን በቴሌቭዥን እናያለን። በአነስተኛና ጥቃቅን እየተደራጁ የኮብል-ስቶን ድንጋይን እያናገሩ ያሉ ወጣት ምሁራንም በታሪክ መዝገብ ላይ እየሰፈሩ ይገኛል።
ኦቦ ሌንጮ ታሪክ የሚሉን እንዲህ አይነቱን ድራማ እንደማይሆን እርግጠኞች አይደለንም። እኝህ የፖለቲካ መሪ ታሪክ መስራት ከነበረባቸው ግዜው አሁን አይደለም። በሽግግሩ ዘመን 20 ሺህ ጦር እና 20 መቀመጫ ይዘው በነበሩበት ጊዜ ለዚህ እድሉ ነበራቸው። ያንን እድል ይዘው ታሪክ ከመስራት ይልቅ ድርጅታቸው ጥቁር ነጥብ ጥሎ ነበር ያለፈው። አቶ ሌንጮ ታሪክ መስራት ከነበረባቸው በሽግግሩ መንግስት የኢትዮጵያ መሪ ሆነው በተመረጡ ግዜ ነበር። በወቅቱ ምን ነበር ያሉት? “በዚህ ላይ አልተዘጋጀሁበትም።” ሲሉ የእድሉን በር ራሳቸው ዘጉት። በርግጥ ያን ጊዜ ከኦሮሚያ የመገንጠል አዙሪት ውስጥ አልወጡም ነበር። ትልቅ ህዝብን ይዘናል እያሉ፤ የመገንጠል ጥያቄን ሲያነሱ በአለም ላይ የመጀመሪያዎቹ ብቻ አይደሉም። የኦሮሞን ህዝብ በፖለቲካ አናሳ ማድረጋቸው የታያቸውም ከ40 አመታት በኋላ መሆኑ ነው። በዚያን ወቅት ኢትዮጵያን መምራት እንችላለን ለማለት በራስ መተማመን አልነበራቸውም። አንድ ሰው አንድ ድምጽ በሚል መርህ ምርጫ አድርገው ከመጓዝ ይልቅ፤ እንደ አናሳ ጎሳ “መገንጠል አለብን” የሚል ያታሪክ ስህተት ውስጥ ነበሩ።
ከኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ወጥተው የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባርን መመስረታቸው ከታሪክ ተወቃጭሽነት ሊያድናቸው ይችላል ። ይህንን በማድረጋቸው የሰማይና የምድርን ያህል ርቆ የነበረውን የፖለቲካ መስመር ሊያጠበው እንደሚችል ግልጽ ነው። ዛሬ የመገንጠልን ጥያቄውን ውድቅ አድርገው ለዲሞክራሲና ለፍትህ መታገል መምረጣቸው ታሪክ ሰሪ ሊያደርጋቸው አይችልም። ይህ ሊሆን የሚችለው ለውጥ አምጥተው ፍትሃዊ ስርዓት ማስፈን ሲችሉ ብቻ ነው።
ሌንጮ ለታ አዲስ አበባ በመግባት ታሪክ እሰራለሁ ሲሉ ይህ የመጀመርያቸውም አይደለም። እ.ኤ.አ. 1993 የስራ ባልደረባቸውን ከከርቸሌ ለማስፈታት አዲስ አበባ ዘው ብለው ገብተው ነበር። እኝህ ሰው ሲገቡ ቦሌ ላይ ልዩ አቀባበል ተደረገላቸው። በብረት ተጠፍረውም ከርችሌ ተወረወሩ። በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ ተካሂዶ በነበረው የግዮኑ የሰላም እና እርቅ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ሲገቡ የታሰሩ ልኡካንን እዚያው ተቀላቀሉ።
ሌንጮ በዚያ ሰዓት ታሪክ ይሰራሉ ብለን ጠብቀን ነበር። ግን ይቅርታ ጠይቀው ከእስር ለመውጣት አንድ ሳምንትም አልፈጀባቸውም። በወቅቱ ከአቶ ሌንጮ ለታ ጋር ረጅም ቃለ-መጠይቅ አድርጌ ይህንን ታሪክ በማሳትመው ጋዜጣ ላይ ለህዝብ ይፋ አድርጌዋለሁ። እርግጥ ነው። የሌንጮ ለታ ፖለቲካ እውቀት የሚደነቅ ነው። በፖለቲካ ብስለታቸውና ትንተናቸው ከማደንቃቸው የፖለቲካ ሰዎች አንዱ ናቸው። ፖለቲካ ማወቅ እና ህዝብን መምራት ግን በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ብዙውን ግዜ የሰዎችን የፖለቲካ ብቃት የምንለካው በንግግር ችሎታው ብቻ ነው። ጥሩ የፖለቲካ መሪ አስተዋይም መሆን አለበት። የመሪ አስተዋይ አለመሆን ደግሞ ችግር የመፍታት ብቃታ ማጣቱን ነው የሚያሳየን። ኦነግ ከ40 አመታት በላይ በትግል ላይ እንደሆነ ይነገረን እንጂ ድርጅቱ ድል አድርጎ አይተን አናውቅም። የሽግግሩን መንግስት ላይም ቢሆን የተገኘው በድል አድራጊነት ሳይሆን ከህወሃት እና ከሻእቢያ ጥሪ ተደርጎለት ነበር።
በአሁኑ የአዲስ አበባ ጉዞ ሌንጮ እንደቀድሞው ልዩ አቀባበል ላይገጥማቸው ይችላል። በእርግጠኝነት ለመናገር ከጉዞው በፊት አንዳች ቅድመ ሁኔታዎች ወይንም ስምምነቶች ይኖራሉ። ይህ ካልሆነ ግን እኝህን ሰው በቀይ መስመር ላይ ማስቆም ወይንም ደግሞ ማኖ ማስነካቱ አይቀሬ ነው። እሳቸውን ቀይ መስመር ላይ ለማቆስም በጣም ቀላል ነው። የበደኖው፣ የዋተሩና የአርባጉጉ ፋይሎች እየተመዘዙ ማውጣት ብቻ ይበቃል። አልያም ቦሌ ላይ እነ ዋልታ ብቅ ብለው በካሜራ ይቀበሏቸዋል። ልማቱን እንዲያደንቁ ይጠየቃሉ። በእስር ያሉ ወገኖችና “ሽብርተኞች”ን ማውገዛቸውም የግድ ነው። በዚህ መስመር ላይ ከሄዱ “አባ ጸበል ይርጩን” ብለው እንደገቡት እንደነ ስም አይጠሬ ተዋርደው ይመለሱና የፖለቲካ ሞትን ዳግም ይቀምሷታል።
ለእንደዚህ አይነቱ “ልማታዊ” የተቃውሞ አስተሳሰብ ሳይገዙ ታሪክ መስራት ከተቻለ ግን ተአምር ይሆናል። ለማንኛውም መልካም ጉዞ…
ክንፉ አሰፋ

lørdag 1. februar 2014

ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነን ለነፃነት መታገል ያስፈልጋል!!

ቃልኪዳን ካሳሁን (ከኖርዌ)

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያዊያን በመላው አለም እንደሚኖሩ ይታውቃል። ከኦሮሚያ ይሁን ከአማራ፣ ከሶማሌ፣ ከደቡብ ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል፣ ድሬ . . . . . . .. ብቻ ከየትም ይምጡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የስደት መንሾ “በፖለቲካ አልያም የተሻለ ህይወት ፍለጋ” ከመሆን አይዘልም።
(በሀገሩ መኖር ማን ይጠላል . . . . . . . )Kalikidan
ብዙ ጊዜ የማስበው ታዲያ ኢትዮጵያውያኑ በሰው ሀገር ሲኖሩ እንዳውም ከሀገር ውስጥ የበለጠ አንድንትና መግባባት ወይም አብሮ የመኖር ስሜት ይኖራቸዋል። በሰው ሀገር የመኖርን የህይወት ትግል ለመላመድና ለማሸነፍም ከሀገር ልጅ የበለጠ አለኝታ፣ አይዞህ/ሽ ባይ እና አጋዥ የለምና። በተለያዩ አጋጣሚዎች የምንሰማው ግን ከዚህ በተቃራኒው የሆኑ እውነታዎችን ነው። በጥርጣሬ መተያየት፣ የብሄርና የፖለቲካ ክፍፍል………ሌላም ሌላም።
እርግጥ ነው ሁላችንም አንድ አይነት አቋም ሊኖረን አይችልም፡ ከመሰረታዊ ጉዳዮች በስተቀር በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የግድ ተመሳሳይ ሀሳብ እንዲኖረንም አይጠበቅም። የተለያየ የፖለቲካ አቋም ሊኖረን ይችላል፣ የተለያዩ ብሄሮች ልጆችም ልንሆን እንችላለን፣ ኢትዮጵያውያን በመሆናችን ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች በህልውናችን ላይ አንዳች ጥላ ማጥላት የለባቸውም። ደግሞም ከተቀራረብን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሊታረቁና ሁላችንንም የሚያስማሙ ሀሳቦችን ለመፍጠር ይችላል። የአፍሪካ የነፃነት ምሳሌ የሆንን ዜጎች ህብረ ብሄራዊ ውበታችንን በእያንዳንዳችን ማንነታችን ላይ ካለው ኢትዮጵያዊነታችን ጋር የተጣበቁ የጋራ ተቀፅላዎችችን (stereotypes) በማጥፋት የትም ቦታ አንገታችንን ቀና አድረገን ለመኖር ምቹ ሁኔታዎችን ልንፈጥርበት ይገባል።
ልዩነቶቻችን በማቻቻል የትም ይሁን የት በአንድነት መስራቱ ለዜጎቿ ለኑሮ ምቹ የሆንች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዳግም ኢትዮጵያን ታላቅ ለማድረግ ያስችለናል። ይህም በቅርቡ እውን እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። ይኸው ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስተዳድረው ወያኔ/ህውሃት የህዝብ መብት በመንቀፍ፣ ዘረኝነትን በማስፋፋት፣ ሀገርን በመከፋፈል፣ ጎሰኝነትን በማስተማር፣ ሀገር በመዝረፍ፣ ሀገርን በመሸጥ፣ ሰውን ከሚኖርበት ቅዬ በማፈናቀል፣ በመቻቻል እንዳይኖር በማድረግ፣ ዘር ከዘር ጥላቻን ማስፈን ቀጥሎበት ሃያ ሁለት ዓምታትን አስቆጠረ። እስከመቼ ይኸን ነገር ዝም ብለን ማየት እንችላለን።
እዚህ ጋር የሌሎች ሀገራት ዜጎችን በሚያስቀና መልኩ አብሮ የመኖርና የመተባበር ባህልና ማህበራዊ ህይወት ያላቸው ባህር ማዶ አደር ኢትዮጵያውያን እንዳሉ መዘንጋት የለበትም። ይሁንና እነሱም ቢሆን እነዚህን መሰል በኢዮጵያውያን እህትና ወንድማማቾች መካከል እየተፈጠረ ያሉ ችግሮች ለመፍታት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።
ነፃነታችንን የቀሙን የወያኔ ዘረኞች ነፃነታችንን እንደቀሙን ለረዥም አመታት ለመግዛት እንዲመቻቸው በዘር፣ በቋንቋ፣ በክልልና በሃይማኖት ከፋፍለውን ከሃያ አንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የጀመሩትን እስራት፣ ስደት፣ ግድያና ዝርፍያ አሁንም እንደቀጠሉ ነው። የወያኔ ዘረኞች ነፃነታችንን ቀምተው እየገዙን ቢሆንም ገዛናቸው ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ዜጎች ነፃነታቸውንና መብታቸውን እንዳይጠይቁ አፋቸውን ያዘጋሉ፣ አንዱ ለሌላው እንዳይቆም ሀገር፣ ባንዲራና ኢትዮጵያዊነት የሚባሉ ትላልቆቹን የጋራ እሴቶቻችንን በየቀኑ ያፈረሳሉ።
ይህ የሚያሳየን ዜጎችን ትልቅ ተስፋ ይዘው ቤተሰብ መስርተው ለራሳቸውና ለሀገራቸው የሚኖሩበት ጊዜ እየጠፋ ተስፋ መቁረጥ፣ ስደትና የመከራ ኑሮ ዘመን እየከበበን መምጣቱ ነው።
ይህ ከሆን የነገዋን የነፃነት፣ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ ባለጸጋ ኢትዮጵያን ለማየት እያንዳንዱ ዜጋ በቻለው አቅሙ ሁሉ ጠንክሮ በመታገል እና ከራሱ ባለፈ ሌላው ዜጋ የነፃነት ትግሉን ጎራ እንዲቀላቀል ብሎም የዚህ ትግል ባለቤት እንዲሆን ያስፈልጋል። የሀገራችን ህዝብ የነፃነት ችቦ አቀጣጣይ የትግሉ አካል በመሆን መስራት እንጂ ከቶ ሌላ አካል፣ ሌላ ሃይል መቶ ነፃ ያወጣኛል በሚል በባርነት እየተገዛ መጠበቅ የለበትም። ነፃነትና ዴሞክራሲ በችሮታ አሊያም ከሰማይ እንደሚወርድ መና የሚጠበቅ ስጦታ አይደለም። ነፃነት የራስን መስዋአትነት ይጠይቃል።
አለበዚያ “ላም አለኝ በሰማይ ወተትዋንም አላይ”እንዳይሆን ያስፈልጋል።
ነፃነት እኛ ሰዎች በልደት ወደዚህ አለም ስንመጣ አብሮን የሚመጣ የተፈጥሮ ፀጋ ነው። ነፃነት ከሌሎች የምንጠብቀው ወይም ማንንም ስጠን ብለን የማንጠይቀው ፈጣሪ ለእያንዳንዳችን ያደለን በዚህ አለም ቆይታችን ለደቂቃም ቢሆን እንዲለየን መፍቀድ የሌለብን ሀብት ነው። ነፃነታችን እጃችን ላይ ሲኖር በግለሰብ ደርጃ የምንደሰተበት፣ እንዳንቀማ በጋራ የምንጠብቀውና እንደወያኔ አይነቱ ፀረ ህዝብ ሃይል ሲቀማን ደግሞ በጋራ
ታግለን ማስመለስ የሚገባን የግልና የጋራ ሀብት ነው።
ዛሬ ከ22 የወያኔ አመታት በኃላ እኛ ኢትዮጵያውያን በድህነትና በረሃብ የምንጠቃው በዘረኝነት አለንጋ የምንገረፈው፣ የምንሰደደው፣ የምንታሰርውና የምንገደለው ይህንን ፈጣሪ ያደለን ነፃነት የሚባል ሀብት ወያኔ አንድ ሁለትና ሶስት እያለ ሲቀማን አፋችንን ዘግተንና እጃችንን አጥፈን ስለተመለከትን ነው። መፈናቀላችን፣ ስደታችን፣ ውርድታችንና በገዛ ሀገራችን ሁለትኛ ዜጋ ሆኖ መኖራችን እንዲያበቃ ለማድረግ ያለን ብቸኛ አማራጭ
ሌሎች መጥተው ነፃ ያወጡናል ከሚለው አመለካከት ተላቅቀን ነፃነታችንን ለማስመለስ ህዝባዊ ትግሉን መቀላቀል ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ የዘር በትር አለንጋ የሚደርስበት ግርፋት፣ ስቃይ፣ ረሃብ፣ ስደት፣ እንግልት በራሱ በህዝቡ ላይ ነው። ስለዚህ ህዝቡ ራሱ ለራሱ ነፃነት በእምቢ አልገዛም ባይነት የሚነሳበት ጊዜው አሁን ነው። ነፃነትን ከነፃ አውጭዎች በመጠበቅ እስከመቼ የወያኔ የጥይት ሰለባዎች እንሆናለን? ወገን ሁሉ ለራሱ ነፃነት፣ ህልውና ሲል የለውጡ እንቅስቃሴ ታጋይ የመሆን ኢትዮጵያዊ ግዴታውን እንዲፈጽም ጥሪ ማድረግ ይገባል። ለሀገሩ፣ ለማንነቱ መሰዋትነት ለመሆን እንደሚኮራ ሁሉ ሀገሩም በሱ ትኮራለች። ወያኔ በ22 ዓመት ውስጥ የሰራው ወንጅል በወገናችን ላይ እንዲህ በቃላት ተዘርዘሮ አያልቅም። ይህ አልበቃ ብሎን።
ታዲያ ምንድ ነው አንድ ሆንን ከመታገል ፈንታ መለያየትን መረጥን!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10879/